“አንድ በሚያደርገን ላይ ሥንሠራ ሀገር አንድ ትኾናለች፣ ሰላም ትኾናለች፣ ትበጽጋለች” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

12
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎”በመደመር መንግሥት ዕይታ የሃይማኖት መሪዎች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ከእስልምና ሃይማኖት አባቶች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የምንወያየው ያጋጠመውን የሰላም ስብራት ለመጠገን፣ የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ያላቸውን ሚና ለማጉላት እና አንድነትን ለማጠናከር ነው ብለዋል።
እስልምና የሰላም ሃይማኖት መኾኑን ተናግረዋል። መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሃይማኖት አባቶች ጋር እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶችም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሥራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች ትውልድን የመገንባት ድርሻቸው ጉልህ መኾኑንም አንስተዋል። የሃይማኖት ተቋማት የዕድገት፣ የታሪክ እና የሰላም መሠረቶች መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ቤተ ዕምነቶች ለሰላም መረጋገጥ እና ለማኅበራዊ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ለሀገር አንድነት፣ ፍቅር እና ሰላም እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
በዜጎች መካከል መግባባት እንዲፈጠር፣ ሀገረ መንግሥት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መኩሪያ የኾኑ ታሪኮች እና ቅርሶች የሚቀዱት ከሃይማኖት ተቋማት እንደኾነም አንስተዋል። የሃይማኖት ተቋማት ሀገር እንዲጸና እና እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋጽኦ ሲጫወቱ ኖረዋል ነው ያሉት። የእስልምና ሃይማኖትም ሰላምን የሚሰብክ መኾኑን አንስተዋል።
አሁን ላይ የክልሉ እና የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ በጋራ መሥራት ይገባናል ብለዋል። ሕዝብ ማኅበራዊ መረጋጋት እንዲኖረው፣ መልካም እሴት እንዲገነባ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ብዝኀ ማንነት ያላቸው ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ብዝኀ ማንነት የመለያያ መሣሪያ መኾን የለበትም፣ ይልቅስ የአንድነት፣ የመተሳሰብ እና የኅብረት ምንጭ መኾን አለበት ብለዋል።
ከሚያለያየን ይልቅ አንድ በሚያደርገን ጉዳይ ላይ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል፤ አንድ በሚያደርገን ላይ ሥንሠራ፣ ሀገር አንድ ትኾናለች፣ ሰላም ትኾናለች፣ ትበለጽጋለች ነው ያሉት።
እየተሸረሸረ የመጣውን እሴት ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። መንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንደሚፈለግም አንስተዋል። በጠንካራ ግንኙነት የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በሃይማኖት እና በሃይማኖት ተቋማት መካከል፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በመንግሥት መካከል ጥብቅ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በሃይማኖት ተቋማት እና በሃይማኖት ተቋማት መካከል፣ በሃይማኖት እና በመንግሥት መካከል መቃቃር ካለ ሕዝብ እና ሀገርን እንደሚጎዳ ተናግረዋል።
በውይይቱ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ለሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት የሚሰጥ ውጤት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር ውይይት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ማንነታችን ይከበር አልን እንጅ ከጎረቤቶቻችን ጋር አብረን አንኖርም አላልንም” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች
Next articleምንጩ ያልታወቀ ሃብት ማለት ምን ማለት ነው ?