
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። በዞኑ የቆራሪት ከተማ ነዋሪዎችም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የሚደግፍ፣ የህወሃትን ለዳግም ጦርነት ትንኮሳ የሚያወግዝ እና መንግሥት ያወጣውን የምርጫ ውሳኔ የሚደግፍ እና የሚያመሰግን ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
ሰልፈኞቹ በንቅናቄ በመውጣት ለመንግሥት የሰላም ጥሪ ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ አሳይተዋል። የህወሃትን ዳግም የጦርነት ትንኮሳ በማውገዝ አካባቢያቸው የሰላም እና የልማት ማዕከል እንዲሆን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ደጀንነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም መልእክታቸውን በአደባባይ አስተላልፈዋል።
ህወሃት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ላይ የዳግም ወረራ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም አውግዘዋል።
የቆራሪት ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ የሽወንድም አስፋው ህወሃት በሕግ የተቀመጠውን የመምረጥና የመመረጥ መብት ለማደናቀፍ እየሠራ ይገኛል፤ ከዚህ አይነት ሕገወጥ ድርጊት መቆጠብም አለበት ብለዋል። ከምርጫ ጋር በተያያዘ መንግሥት የወሰነው ውሳኔ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ህልውናውን የሚያረጋግጥበት መኾኑን ገልጸው ምስጋናም አቅርበዋል።
“ትግላችን የእውነትና የፍትሕ፤ ራስን የመኾን ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ሕዝቡም ነፃነቱን አሳልፎ ላለመስጠት ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሆን ሰላምና ልማትን ማስቀጠል፣ የመምረጥ መብቱን በመጠቀም ህልውናውን ማረጋገጥ ይገባዋል ነው ያሉት። ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲኾንም እንሠራለን ቤለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
