
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀሰተኛ መረጃ ዜጎች የተሳሳተ መረጃ እንዲይዙ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ በማድረግ በግለሰብም ኾነ በሀገር ላይ ጥፍት የሚያደርስ ክስተት ነው።
በተለይ እንዲህ ምርጫ በሚደርስበት ወቅት ደግሞ መረጃዎችን ደጋግሞ ማረጋገጥ የግድ የሚልበት ጊዜ ነው። ምክኒያቱም ዜጎች በአካባቢያዊ እና ሀገር አቀፍ ምርጫዎች በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፤ እንዲኹም በማኅበረሰቦች መካከል መከፋፈልን እና መካረርን በማስፋት ለግጭት በር ይከፍታል።
በዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እና በማኅበረሰቦች መስተጋብር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መግታት አስፈላጊ ነው። ችግሩ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እና ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የሲቪክ ድርጅቶች፣ የማኅበረሰብ ትስስር መድረኮች እና መንግሥት ተቀናጅተው የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል።
ዜጎች ስለሚዲያ እና ስለመረጃ ያላቸውን ንቃት እና ግንዛቤ ማሳደግ ሀሠተኛ መረጃ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመግታት አይነተኛ መፍትሄ ነው። ንቃት እና ግንዛቤ ያላቸው ዜጎች ትክክለኛ መረጃ ከየት ማግኘት እንዳለባቸው ያውቃሉ።
ለሀሠተኛ መረጃ ያላቸውን ተጋላጭነት ይቀንሳሉ። ይህም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲወስኑ ያስችላቸዋል። በዚህ ረገድ የሲቪክ ድርጅቶች ጉልህ ሚና መጫወት ይችላሉ።
የሲቪክ ድርጅቶች የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እና ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ዜጎችን የማንቃት እና የማስተማር ሥራ መከወን እንዲኹም ሀሠተኛ መረጃን የተመለከቱ ይዘቶች በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ግፊት በማድረግ፣ የነቃ እና ግንዛቤ ያለው ትውልድ እንዲፈጥር የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ፊንላንድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ ሀሠተኛ መረጃን የተመለከቱ ይዘቶችን በሥርዓተ-ትምህርቷ በማካተት እና የተቀናጀ የንቃት እና የግንዛቤ ዘመቻዎችን በማካሄዷ፣ የሀሠተኛ መረጃ ተጽዕኖን በመቋቋም ረገድ በብዙዎች ዘንድ በምሳሌነት ትጠቀሳለች።
በሌላ በኩል እንደ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ቴሌግራም እና ትዊተርን የመሳሰሉ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ይታወቃል።
እነዚህን መድረኮች ትክክለኛ መረጃ የሚያሰራጩ ገጾች እና ቻናሎች በቅድሚያ የመታየት ዕድል እንዲያገኙ በማስቻል፤ ዜጎች ሀሠተኛ መረጃን ሪፖርት የሚያደርጉበትን አካሄድ ቀላል እና በሚረዱት ቋንቋ እንዲኾን በማድረግ እንዲኹም ሪፖርቶችን እና ይዘቶችን የሚከታተሉ በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ የሀሠተኛ መረጃ ስርጭት እንዲቀንስ ኅላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በተመሳሳይ ሚዲያዎች በተቋማቸው ውስጥ መረጃ የሚያጣራ ክፍል በማቋቋም እና ጋዜጠኞቻቸው ስለ መረጃ ማጣራት ሂደት በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማሠልጠን ሀሠተኛ መረጃ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን መወጣት ይችላሉ።
መንግሥት የሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል ያወጣውን ሕግ በአግባቡ እንዲፈጸም የማድረግ ኅላፊነት አለበት፡፡
ከሲቪክ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዜጎች ስለ ሚዲያ እና መረጃ በቂ ንቃት እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማገዝም ይጠበቅበታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
