
አዲስ አበባ: የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በመከበሩ የሴቶች የፓርላማ ተሳትፎ ወደ 41 በመቶ ማሳደግ መቻሉን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ50ኛ ዓመት እንደሚከበር ተናግረዋል። የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓልም አብሮ የሚከበር በመኾኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት በልዩ ሁኔታ ለዘርፉ አጥኝዎች ግብዓት መስጠት በሚያስችል መልኩ ይከበራል ነው ያሉት።
ካለፉት 50 ዓመታት በፊት በሴቶች በፖለቲካ ተሳትፎ አንዲት የፓርላማ አባል እንደበረች ያስታወሱት ሚኒስትሯ
መከበር ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ግን 41 በመቶ የፓርላማ ተሳትፎ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
50 በመቶ የካቢኔ ድርሻ እንዳላቸቸውም ተናግረዋል።
ይህም የሴቶች ቀን በመከበሩ እና ትኩረት በመሰጠቱ የተገኘ ስኬት መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዲኾኑ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል። ሴቶች በትምህርት እና በጤና ተሳትፎ ያለቸው ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪ ያለዕድሜ ጋብቻን መከላከል እና የሴት ልጅ ግርዛትን መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በዓሉ “50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት ለቀጣይ አንድ ወር እንደሚከበርም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አንዷለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
