ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር በሴቶች እኩልነት እና ነጻነት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

1


ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከሚዲያ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።

‎በመድረኩ የተሳተፉት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አስማረች ምስክር ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች ከጭቆና እና ከብዝበዛ ነፃ ኾነው በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲኾኑ መሠረት የጣለ ነው ብለዋል።

‎መሻሻሎች ቢኖሩም፣ የሴቶች ተሳትፎ ገና ከሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ገልጸዋል። አሁንም ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ጠቁመዋል።

‎ሌላው ተሳታፊ የአሚኮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር መሰረት አስማረ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበሩ በሴቶች እኩልነትና ነጻነት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል። ለውጡ በአንዴ የማይታይ ቢኾንም በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ የመጡ ብዙ ለውጦች እንዳሉ ገልጸዋል።

‎ሚዲያዎች ቀድመው ያያሉ፤ ጉዳዮችን በማመዛዘን የሴቶች ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ በማድረግ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል። ሃሳቦችን በነጻነት እና በአውዳቸው በማንጸባረቅ ለውጡ ከፍተኛ እንዲኾን ሴቶች ወደ አደባባይ ወጥተው የሀገራዊ ለውጡ ተሸካሚ፣ የኢኮኖሚ ለውጥ አብዮተኞች እንዲኾኑ ሚናቸው ትልቅ መኾኑን ነው የገለጹት።

‎የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶች በኢኮኖሚ እንዲጠናከሩ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ መሠራቱን ተናግረዋል። ሴቶች በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ መደረጉንም ገልጸዋል።

‎የሚዲያ አካላት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የታዩ ለውጦችን በማሳየት እና ቀሪ ማነቆዎችን በመለየት ግንዛቤ ለመፍጠር ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
‎‎

Previous articleግብርናው ከበሬ ትክሻ ወደ ትራክተር እርሻ እየተሸጋገረ ነው።
Next articleበእጣን እና ሙጫ ምርት ከ5 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።