
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ እና በኢትዮጵያ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በአማራ ክልል ለሚዲያ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) የሴቶች የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መብቶች እንዲከበሩ የተደረገ ረጅም የትግል ጉዞ የሚዘከርበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል።
ዕለቱ ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ሲከበር በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቀነስ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ኾኖ መቆየቱን ተናግረዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በእጥፍ እንዲጨምር መደረጉንም ገልጸዋል።
የዘንድሮው መሪ መልዕክት ”የ50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” የሚል ነው። ይህም ሴቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን አካላትም የሴቶችን ድምጽ በማጉላት ሚናቸው ከፍተኛ በመኾኑ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመሞገት እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በሀገሪቱ በቁጥር ግማሽ የሚኾኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች ናቸው፤ በተግባርም ከቤት እስከ ተቋማት ከፍተኛ ሚና አላቸው ነው ያሉት።
የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ክልሉን በልማት፣ በሰላም የተሳካለት ለማድረግ፣ የሴቶችን የልማት እና የፖለቲካ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል። ይህንን ለማድረግም የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚናው ከፍተኛ እንደኾነ አንስተዋል።
በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ያሉ የተዛቡ አሰተሳሰቦችን በማረም በኩል ሚዲያ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።
ለሰላም መረጋገጥ እና ለምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ኀላፊው በቀጣዩ ምርጫ ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
