
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ዓለሚቱ ለማ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። የካንሰር በሽታ ተጠቂ በመኾናቸው የጨረር ሕክምና እንዲያገኙ በሐኪሞች ይታዘዛሉ። ኾኖም በጎንደር ከተማ የጨረር ሕክምና ባለመኖሩ ወደ አዲስ አበባ የጨረር ሕክምና ለማግኘት ይሄዳሉ።
ለወራት ሕክምናውን ለማግኘት ቢጠባበቁም የታካሚዎች ቁጥር በመብዛቱ ከ150 ሺህ ብር በላይ ለተለያዩ ጉዳዮች ወጭ አውጥተው ሕክምናውን ሳያገኙ ቀርተዋል።
በመካከል ግን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ብቸኛ የኾነውን የጨረር ሕክምና መጀመሩን በመስማታቸው ወደ ጎንደር ተመልሰው የጨረር ሕክምና ሲከታተሉ ነው ያገኘናቸው። የጨረር ሕክምና በአካባቢው ባለመኖሩ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ወጭ እና እንግልት ተዳርገው እንደነበር አስታውሰዋል።
በሰላም እጦቱ ምክንያትም ለአላስፈላጊ የትራንስፖርት ወጭ መጋለጣቸውንም ጠቁመዋል። ከሕመማቸው ባሻገር ከፍተኛ ወጭ እንዲያወጡ በማድረግ የኢኮኖሚ ጫና እንዳደረሰባቸውም አስታውሰዋል።
በአካባቢው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጨረር ሕክምና መጀመሩ የኢኮኖሚ ጫናን የሚቀንስ እና በቶሎ ሕክምናውን ለማግኘት የሚያስችል በመኾኑ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጨረር ሕክምና ባለሙያ ዳንኤል አስማረ በአማራ ክልል ብቸኛው የጨረር ሕክምና ማዕከል መኾኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከክልሉ አልፎ ከትግራይ፣ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እና አልፎ አልፎም ከሱዳን ለሚመጡ የሕክምና ፈላጊዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ለጨረር ሕክምና የሚመጡ ሕሙማን ሲቲ ሲሙሌሽን ክፍል ላይ የተለያዩ ሕክምናዎች እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ሲቲ ሲሙሌሽን ክፍል የታካሚው የካንሰር አይነት የሚለይበት መኾኑን ያነሱት ባለሙያው ታካሚዎች ለጨረር ሕክምናው ዝግጁ የሚኾኑበት ክፍል ነው ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አማረ የሽጥላ
በደም ውስጥ የሚሰጥ (ኬሞቴራፒ)፣ በሚዋጥ የሚሰጥ ክኒን፣ የቀዶ ሕክምና እና የጨረር ሕክምና የካንሰር የሕክም እና አማራጮች መኾናቸውን ገልጸዋል።
የጨረር ሕክምና ካንሰሩ የተነሳበትን አካባቢ ለመቆጣጠር የሚያገለግል ዋነኛ የሕክምና አማራጭ መኾኑንም ተናግረዋል። ካንሰር አራት ደረጃዎች እንዳሉት ያነሱት ዶክተር አማረ ከደረጃ አንድ እስከ ሦሥት ያሉ ታካሚዎችን ሙሉ ለሙሉ ከሕመማቸው ለማዳን እንደሚሰጥም አንስተዋል።
ደረጃ አራት ላይ ለደረሱ ታካሚዎች ሕመሙን የማስታገስ ሕክምና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ለማኅጸን በር ካንሰር፣ ለጡት ካንሰር፣ ለአዕምሮ ካንሰር፣ ለአጥንት ካንሰሮች እና ለሌሎችም የካንሰር አይነቶች ፍቱን የሕክምና አማራጭ መኾኑንም አንስተዋል።
የጨረር ሕክምና እንደ ካንሰሩ ኹኔታ ከአንድ ቀን እስከ 35 ቀን ድረስ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
ታካሚዎች የጨረር ሕክምና በሚወስዱበት ወቅት የሕመም ስሜት እንደሌለውም ተናግረዋል። አገልግሎቱ ከጀመረ ወራቶች ማስቆጠሩን ያነሱት ዶክተር አማረ 260 ታካሚዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ታካሚዎች በካንሰር በሽታ መጠቃታቸውን ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት የካንሰር ደረጃው ሳያድግ ሕክምና በማግኘት በቶሎ እንዲያገግሙም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
