በግጭት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚሠሩ ሥራዎች በትኩረት ሊከናወኑ እንደሚገባ ተገለጸ።

8

 

አዲስ አበባ፡ የካቲት 24/2018ዓ.ም (አሚኮ) በግጭት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የመጠገን፣ የማቋቋም እና የማልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲኾኑ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) አሳስበዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ማሳሰቢያውን የሰጡት በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች የመልሶ ማልማት እና ማቋቋም ፕሮጀክት አተገባበር ግምገማ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በሚመክር መድረክ ላይ ነው።

ሚኒስትሯ ፕሮጀክቱ በግጭት የተጎዱ ዜጎችን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ያለመ መኾኑን ገልጸው መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች ተጎጂ የኾኑ ዜጎች እኩል የልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ተነድፎ እየተተገበረ ያለው የፕሮጀክቱ ንዑስ ክፍል ሁለት ተግባራዊ እየኾነ መኾኑን ጠቁመው የሴቶችን ጥቃት ትርጉም ባለው መልኩ ማስቆም ዋነኛው ግብ መኾኑን ተናግረዋል።

ዕቅዱ ስኬታማ እንዲኾን በቁርጠኝነት፣ በቅንጅት እና በፍጥነት መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ሚኒስትሯ በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ያሉ አበይት ተግባራትን ዘርዝረዋል።

በዚህም መሠረት፦

👉በአምስት ክልሎች ውስጥ የ”አንድ ማዕከል” አገልግሎት እና የ49 የመጠለያ እና የማገገሚያ ቦታዎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

👉የ42 የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ማዕከላት እድሳት እና የግብዓት ማሟላት ሥራ እየተሠራም ነው።

👉ለ5 ሺህ ተጎጂ ዜጎች የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ሲኾን የ245 የመንደር ቁጠባ እና ብድር ማኅበራትን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነም ነው።

👉ርህራሄ የተሞላበት እና ተጠቃሚዎችን ማዕከል ያደረገ እንክብካቤ እንዲሰጥ ከ3 ሺህ በላይ ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

👉በተጨማሪም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል የሚያስችል የኅብረተሰብ ንቅናቄ የመፍጠር ሥራም በትኩረት እየተሠራ ነው።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት 300 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲኾን አፈጻጸሙም በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተሸፈነ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአፋር እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተግባራዊ እየኾነ ሲኾን በምክክር መድረኩ ላይም የእነዚህ ክልሎች ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ መሣሪያዎች በሆስፒታሎች ተደራሽ እየኾኑ ነው።