በወንጀል የተገኘ እና ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን የማስመለስ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው።

7

 

ባሕርዳር፡ የካቲት 24/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል ባለድርሻ የመንግሥት ተቋማት በወንጀል የተገኘ እና ምንጩ ያልታወቀ የንብረት ማስመለስ ሥራዎችን በቅንጅት እና በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ላይ በጋራ በመምከር ተፈራርመዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በወንጀል የተገኘ እና ምንጩ ያልታወቀ ንብረት እንደ ሀገር እና እንደ ክልል እየተበራከተ በመምጣቱ የሀገር እና የክልሉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ኹኔታ እየተጎዳ እንደኾነ ተናግረዋል።

ይህን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አሁን ላይ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 ወጥቶ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑን ነው የጠቀሱት።

ቀደም ሲል በወንጀሉ ብቻ መጠየቅ እና ማስቀጣት ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ እንደነበርም አንስተዋል። አሁን ላይ ደግሞ አዋጁ ወደ ኋላ 10 ዓመት ሂዶ ገቢው ትንሽ ነገር ግን ምንጩ የማይታወቅ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ሃብት አካብተው እየተጠቀሙ ያሉ ሰዎች ካሉ በሕጉ መሠረት የማስመለስ ሥራ እንደሚሠራ ነው የጠቀሱት።

በወንጀል ፍሬ የተገኘ ሃብት ካለም ከእነትርፉ የማስመለስ ሥራ ይሠራል፤ በወንጀል ሕግ እንዲቀጡም ይደረጋል ብለዋል።

ተግባሩ ውጤታማ እንዲኾን ደግሞ ሥራው በቀጥታ የሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል ተቋማት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። ስምምነቱ በክልል ደረጃ ብቻ የሚያልቅ ሳይኾን ወደ ዞን እና ወረዳዎች እንደሚወርድም ጠቅሰዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ካሳሁን ደመመ ገቢዎች ታክስ የሚሠበሥብ ተቋም ከመኾኑ ጋር ተያይዞ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ በርካታ ችግሮች እያጋጠሙ እንደኾነ ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ወንጀሎች ላይ ውይይት መደረጉ እና ሕግ መውጣቱ ደግሞ የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለማስቆም አይነተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት። የታክስ አሥተዳደሩንም የተሻለ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። ለዚህም የቅንጅታዊ አሠራር ስምምነቱን በቁርጠኝነት ለመፈጸም ተቋሙ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ደግሞ አላግባብ የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረት መዝረፍ እና መመዝበር ለሀገር ደኅንነት እና ለሕዝቦች አንድነት ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል። ችግሩ ደግሞ በተግባር እየታየ እንደኾነ ነው የጠቆሙት።

እስካሁን በነበረ የመንግሥት ንብረት የማስመለስ ሂደት ፖሊስ በተለያየ የፋይናንስ የወንጀል ማዕቀፎች ላይ ሥራዎችን ሲሠራ እና ትግል ሲያደርግ እንደቆየ ተናግረዋል።

የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው እና ተባብረው ችግሩን መከላከል፣ የተደበቀን ንብረት ማስመለስ እና ተጠያቂ ማድረግ ላይ ከሠሩ ደግሞ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፤ ፖሊስ ደግሞ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወርሃ ጥር እና የካቲት 𝟐𝟎𝟏𝟖 የሥራ ትግበራዎች ማጠቃለያ፤
Next articleከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ መሣሪያዎች በሆስፒታሎች ተደራሽ እየኾኑ ነው።