
ባሕር ዳር: የካቲት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ ዕዝ በተሠማራባቸው በሰሜን ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በማዕከላዊ ጎንደር አዋሳኝ ቀጣናዎች 135 ጽንፍ ይዘው ሲዋጉ የነበሩ ሲደመሰሱ 68 የሚሆኑት መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡
በስምሪቱ 46 ኤ ኬ ኤም/ክላሽ፣ 43 የቃታ መሳሪያ፣ አንድ ፒ ኬ ኤም/መትረየስ፣ አንድ ስናይፐር፣ 5 ቦምብ እና ተተኳሾች በቁጥጥር ሥር እንደዋለም ተመላክቷል፡፡
ሠራዊቱ ሰሞኑን በዳንግላ ዙሪያ ጭሮ፣ ፋግታ፣ ደብረ ወርቅ፣ ድማማ አንገረብ፣ በዋዝ እና ደብረ ዘይት አቅጣጫ በተደረገው ስምሪት 50 ጽንፈኞች ሲመቱ፣ 39 መቁሰላቸውንም ገልጿል።
በሰከላ ወረዳ ሱርባ ቀበሌ የተሠማራው ሠራዊቱ ባደረገው የተጠና ኦፕሬሽን 47 ጽንፈኞች እንዲደመሰሱ ሲያደርግ 14 ቆስለዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር አለፋ ወረዳ ሻውራ ከተማ አቅራቢያ በተወሰደው ርምጃም 38 የጥፋት ኀይሎች ሲደመሰሱ 15 ቆስለዋል፡፡
ሠራዊቱ ባልተሰማራባቸውና ራቅ ባሉ ቀበሌዎች ሕዝብን እየዘረፈ ሲያስጨንቅ የነበረው ታጣቂ ቡድን በደረሰበት ክፉኛ ምት ሙት እና ቁስለኛ መሆኑን ዕዙ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከውጭ የተሰጠውን ተተኳሽ ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ለማሳለፍ ያደረገው ጥረት አባድራ ላይ በደረሰበት ክፉኛ ምት ጽንፈኛ ቡድኑ እንደተበተነም ተጠቅሷል፡፡
ዘራፊው ቡድን ሰሞኑን በህይወት አለሁ ለማለት ያለ የሌለውን ተተኳሽ ተሸክሞ ሰርጎ ለማለፍ እና ለማስከፈት ያደረገው ሙከራ መንገድ ተዘግቶበት ሳይሳካለት ሙት እና ቁስለኛ መሆኑን የምሥራቅ ዕዝ ገልጿል፡፡
ምሥራቅ ዕዝ ከመከላከያ ጋር በፈጠረው የተኩስ ቅንጅት አማካኝነት ከየካቲት 13/2018 ዓ.ም ወዲህ ከተደመሰሱት የጽንፈኛ አመራሮች መካከል ንብረት መላኩ የተባለ በነሱ ሻለቃ አዛዥ፣ ብርሀኑ በላይነህ – ሻለቃ ዘመቻ፣ አለማየሁ ጌቴ -ሻለቃ መሪ፣ አስቻለው በውሉ-ክፍለጦር ሎጀስቲክስ፣ ምህረቴ አየለ የተባለሻለቃ ዘመቻ እንደሚገኙበትም አስታውቋል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ ብርቁ ደሴ የተባለ ክፍለ ጦር ዘመቻ፣ ነጋ ባቡቾ – ኮር ፖለቲካ ሀላፊ፣ ዘሪሁን ( ጊዎርጊስ ) -የተባለ የክፍለ ጦር ዘመቻ ኀላፊ ተደምስሰዋል፡፡
በዚህ ውጤታማ እና የተጠና ኦፕሬሽን የክልሉ የጸጥታ ኀይል እና ሕዝቡ ያደረጉት ጥረት ጠላት ምንም መደበቂያ እንዳያገኝ፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዳይችል፣ ተስፋ እንዲቆርጥ ፣ እርስ በርስ እንዲጋጭ እና እየከዳ እጁን እንዲሰጥ አስገድዷል ብሏል ዕዙ፡፡
ምሥራቅ ዕዝ ከክልሉ ሕዝብና የፀጥታ ኀይል ጋር በመጣመር የሚያደርገውን ሕግ የማስከበር ተልዕኮ አስተማማኝ ሰላም እስኪመጣ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የምሥራቅ ዕዝ አስታውቋል፡፡ ምንጭ: ምሥራቅ ዕዝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
