የክልሉን የገቢ አሠባሠብ ሂደት ለማሳለጥ አዳዲስ አዋጆች፣ መመሪያዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

4

 

ደብረብርሃን፡ የካቲት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ 103 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

ዕቅዱን ለማሳካት እና የአሠራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከሰሜን ሸዋ ዞን፣ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ከደብረ ማርቆስ እና ከደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለተውጣጡ በየደረጃው ለሚገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በደብረ ብርሃን ከተማ ሥልጠና ሰጥቷል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ግብር መክፈል ለሀገር ዕድገት እና ኩራት መሠረት ይጥላል ብለዋል።

የክልሉን የገቢ አሠባሠብ ሂደት ለማሳለጥ አዳዲስ አዋጆች፣ መመሪያዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መኾኑን ጠቁመዋል።

የተሰጠው ሥልጠናም እነዚህን አዳዲስ ደንቦች በውጤታማነት ለማስፈጸም ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለመሠብሠብ ከታቀደው 103 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ከ50 በመቶ በላይ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የሚገኙ ከ2ሺህ 300 በላይ የገቢ ሠብሣቢ መስሪያ ቤት ሠራተኞች በዚሁ ተግባር ተኮር ሥልጠና ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የሸዋ ቀጣና ጥንታዊ የግብር አከፋፈል ታሪክ ያለው መኾኑን ገልጸዋል።

ከተማዋ ፈጣን ዕድገት እንድታስመዘግብ የገቢ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ለገቢ አቅም ዕድገት ያለውን ፋይዳ አንስተዋል።

በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ የሚገኘውን የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ከወረዳው ብቻ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የተሻሻለውን የገቢ ግብር አዋጅ፣ የቴምብር ቀረጥ እና ሌሎች መመሪያዎችን አስመልክቶ ሥልጠናውን የወሰዱ ባለሙያዎች ሥልጠናው ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

በሙያው ብቁ፣ በሥነ-ምግባሩ የታመነ ጠንካራ መሪ እና ሠራተኛ እንዲኖር ለማድረግ ሥልጠናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ገንዘብ ታደሰ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎችን በመከላከል የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል።