ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎችን በመከላከል የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል።

6

 

ባሕርዳር፡ የካቲት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና በክልሉ የሚገኙ የፌደራል ባለድርሻ የመንግሥት ተቋማት በወንጀል የተገኘ እና ምንጩ ያልታወቀ የንብረት ማስመለስ ሥራዎችን በቅንጅት እና በትብብር ለመሥራት እየመከሩ ነው።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም አሁን ላይ ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች እንደ ሀገር እና እንደ ክልል እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ወንጀሎች ደግሞ የሀገር እና የክልሉን ኢኮኖሚ እና ጥቅም በከፍተኛ ኹኔታ እየጎዱት ነው ብለዋል። ወንጀሎቹን በመከላከል እና በመቆጣጠር ደግሞ የሀገር እና የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማዳን እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በርካታ ሰዎች ምንጩ ባልታወቀ ንብረት ከገቢያቸው ጋር ያልተመጣጠነ የንብረት ባለቤት እየኾኑ እንደኾነም አንስተዋል። ይህ ደግሞ የሀገሩቱን እና የክልሉን የግብር ሥርዓት፣ የውጭ ምንዛሬውን እና የገንዘብ ሥርዓቱን ችግር ውስጥ ይጥለዋል ብለዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ደግሞ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 ወጥቶ ሥራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል። በዚህ አዋጅ መሠረት ከንብረት ማስመለስ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የፍትሕ ሚኒስቴር እና በክልሎች ደግሞ የክልል ፍትሕ ቢሮዎች መሥራት እንዳለባቸው በአዋጁ ላይ በግልጽ መቀመጡን አንስተዋል። እንደ ፍትሕ ቢሮ አዋጁ ከመውጣቱ በፊትም ወደ ሥራ መገባቱን ነው ያስታወሱት።

ጉዳዩ ውስብስብ፣ ከስውር ወንጀሎች ጋር የተሳሰረ እና ተሻጋሪ በመኾኑ የበርካታ ተቋማትን ቅንጅት የሚፈልግ እንደኾነም ጠቅሰዋል። ዛሬ ተግባሩን ለማሳካት ቁልፍ ሚና ያላቸው የፌደራል እና የክልል የመንግሥት ተቋማት የስምምነት ሰነድ ላይ የፊርማ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።

ስምምነቱ ሦሥት ቁልፍ ዓላማዎች አሉት ያሉት የፍትሕ ቢሮ ኀላፊው በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ንብረት ማስመለስ የሚያስችል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር መፍጠር አንዱ ዓላማም እንደኾነ ተናግረዋል። በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ንብረት በማስመለስ የመንግሥትን እና የሕዝብን ንብረት ከምዝበራ ማዳን ደግሞ ሁለተኛው ዓላማ ነው ብለዋል። ሦሥተኛው ዓላማ ከንብረት ምዝበራ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የሰላም እና የደኅንነት ስጋቶች መቀነስ መኾኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህን ዓላማዎቸ ለማሳካትም ተቋማት የጋራ እና የተናጠል ኀላፊነታቸውን በመረዳት በቅንጅት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ስጋት አይኾንም።
Next articleየክልሉን የገቢ አሠባሠብ ሂደት ለማሳለጥ አዳዲስ አዋጆች፣ መመሪያዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።