
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 130ኛው የዓድዋ ድል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።
በክብረ በዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የዓድዋ ድል ለአፍሪካ እና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ጎህ የፈነጠቀ፣ የሰብዓዊ ክብር እና ሞገስ ያጎናጸፈ፣ የኢትዮጵያውያን ሕልቆ መሳፍርት ጀግንነት በዓለም አደባባይ ያበሰረ ታሪካዊ ገድል ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል የወንዶች ጀግኖች ውሎ ድል ብቻ ሳይኾን፣ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ብልሃት፣ የሀገር ፍቅር እና ጽናት የገለጠ የታሪክ ምዕራፍ መኾኑን ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል የእሳቤ ጉልበቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል። የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መቃኛ መኾን እንዳለበት አንስተዋል። የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነትን ሲያገዝፍ፣ የቡድን እሳቤን በአግባቡ ከርክሞ የሚይዝ ነው፤ ዓድዋ አጉራ ጠን ፖለቲካን ይጠየፋል፤ ጠብ አጫሪነትን እና መከፋፈልን ያጨምታል፤ ሌብነትን፣ ውስልትናን እና ሀኬትን ይንቃል፤ የዘመኑ ዓድዋ አረዳድም ቁልፉ ጉዳይ ይህ ነው ብለዋል።
ዓድዋ ሁልጊዜም በጦርነት ለማሸነፍ ለሚፈልጉ ሁሉ አስተማሪ የኾነ ታላቅ መካነ ዕውቀት መኾኑን ገልጸዋል። ዓድዋን ስናስብ በአዕምሯችን የሚመላለሰው ጀግንነት ነው፤ ጀግንነት ደግሞ ሰላምን ማጽናት፣ ሕዝብን መጥቀም እና ሀገርን ማበልጸግ ነው ብለዋል።
የዘመናችን ጀግና የነውጥ ጩኸትን የሚያሰማ ሳይኾን፣ የሀገር ፍቅር፣ የመቻቻል፣ የጥበብ እና አብሮ የማደግን ድምፅ የሚያጎላ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊነት በዓድዋ ሚዛን ሲዘመን ሕይወትን በመለገስ የጸና፣ በላብ የጠነከረ፣ በዕውቀታችን፣ በትዕግሥታችን እና በአርቆ አሳቢነታችን የሚለመልም ሕያው ማንነት ነው ብለዋል።
ዓድዋ ነጻነት የተረጋገጠበት፣ ነጻነትን በድል የተረጎመ ታላቅ ድል መኾኑን ገልጸዋል። አሁን በሚለዋወጠው የዓለም የጂኦፖለቲካ እና የጂኦግራፊ ሂደት ውስጥ የዓድዋን መንፈስ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
በዓለም የተበተኑ ጥቁር ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን የነጻነት ቁጭት እና የእኩልነት መሻታቸውን አባቶቻችን በጦር ሜዳ ጀግንነት እንደመለሱት ሁሉ የዘመኑ ጀግኖች ደግሞ ይህን ጥሪ በሥራ፣ በዕውቀት እና ሀገርን በማሳደግ መመለስ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የዛሬው የዓድዋ ትርጉም ነጻነትን በብልጽግና ማስዋብ፣ ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ አኩሪ ታሪክ መሥራት እና ማስተላለፍ ነው ብለዋል። ዓድዋን ስናስብ አባቶቻችን ለሉዓላዊነታችን የከፈሉትን ዋጋ ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ሰፊ ራዕይንም ጭምር ነው ይላሉ።
በዓድዋ ድል ማግስት የዲፕሎማሲ አንዱ ማጠንጠኛ የነበረው ኢትዮጵያ ከዓለም የምትገናኝበትን እና ወደብ የማረጋገጥ ጉዳይ ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዛሬም እኛ የምንሻው እንግዳ ጉዳይ ሳይኾን ይህኑ የታሪክ መንገድ እና ፈለግ ነው ብለዋል። አስተማማኝ እና ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት መብታችን የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል ነው ብለዋል።
ጥሪውን ልንሸሸው ዝንታለም ብንሞክርም ዝንታለም ከእኛ ሊነጠል የማይችል ሕያው ሐቅ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን ያደረግነውን ተጋድሎ ስናይ ታሪክ ለኢትዮጵያ በጎ ነበር፤ ነገር ግን በአልፎ ሃጅ እና በሰሞንኛ የፖለቲካ ርእዮት ስሌት፣ ኢትዮጵያዊነትን ባልዋጀ ሃሳብ ታሪካችን እና ስትራቴጂካዊ መልሕቃችን መስዋዕት እንድናደርግ ተገደናል ነው ያሉት።
ነገን ማየት እንዳንችል በፖለቲካ ግርዶሽ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቻችንን አሳልፈን ሰጥተናል፤ ስለዚህ ዓድዋ ያስተማረን በሉዓላዊነት ጉዳይ የምንወስደው ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ከታሪክ ትክክለኛ ጎን መቆም እንዳለብን ነው ብለዋል።
ትናንት በዓድዋ አውድማ ላይ የተገኘው ወታደራዊ ድል ዛሬ በኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካ ድል ካልታጀበ ዋጋ እንደሌለው ተናግረዋል።
የሀገራችንን የኢኮኖሚ ጥም የሚረካው፣ የኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ ብሩህ የሚኾነው፣ ኢትዮጵያ በጆኦግራፊ ግርግም፣ በየብስ እግረ ሙቅ አለመታሰሯን ስናረጋግጥ ብቻ ነው ብለዋል።
እንደ ዓድዋ ጀግኖች ሁሉ ለሀገራችን ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። መንገዳችን ደግሞ ሰላማዊ መኾን አለበት፤ የባሕር በር ጥያቄውን የታሪክ እና የፍትሕ ጥያቄ አድርጎ መረዳት ሀሳቡም የዚህ ዘመን ፍላጎት ብቻ ሳይኾን የትውልድ ሕልውና ጉዳይ መኾኑን መረዳት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ልጓም ከሌለው የፖለቲካ ምኞት እና ናፍቆት ይልቅ ለሕዝብ ፍቅር እና ለወገን ሕይወት መለወጥ መጽናት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለውጭ ኃይሎች ዳረጎት ከመማለል ለሀገር እና ለብሔራዊ ክብር መታመን ያስፈልጋል፤ ከዚህ በላይ ጸጋ፣ ከዚህ በላይ ክብር የለም ነው ያሉት።
የዓድዋ ብሩህ መንፈስ ቅጥረኝነትን እንደሚጠየፍም ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊ ለሳንቲም ማተቡን ለባዕድ አሳልፎ መስጠት እንደማይገባውም ገልጸዋል። የቅጥረኝነት አባዜ ያስተዛዝብ ይኾናል እንጂ ኢትዮጵያን አሸንፎ አያውቅም ብለዋል።
ከአፍታ የፖለቲካ ስሌት ይልቅ የሕዝብን ያማከለ፣ ስትራቴጂካዊ እይታ መተለም እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች ማዕከል ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የእድገት ግስጋሴ ለማወክ በየጊዜው የሚመላለሱ ኃይሎችን መግራት ተገቢ መኾኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የመዘመን ጎዳና ላይ የተጋደሙ ካሉ ወይ አልፎ መጓዝ ነው፤ ወይም ተራምዶ መሻገር ነው ብለዋል። ከማያድግ እና ከቆመ ሃሳብ ጋር ላይላቀቁ ውል ያሠሩ ካጋጠሙም ደግሞ ይስተካከሉ ዘንድ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አዲሱ ሃሳብ ሊወለድ አሮጌው ሃሳብ ሊሞት የሚያቆመው የለም፤ ለአዲስ ሃሳብ መትጋት ያስፈልጋል፤ ወደኋላ መመለስ የለብንም ብለዋል።
የዝመናን ሃሳብ የናቀ እና ያነወረ የፖለቲካ ሰው ለምክንያታዊነት ራሱን ተገዥ እንዲያደርግ ብርቱ ትዕግሥት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የምታሸንፈው በልጆቿ ብርታት እና በሃሳቧ ልዕልና ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያን የመገለጥ ዘመን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል። ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊነት ታላቅ ሃሳብ ነው፤ የዓድዋ አደራ ሀገርን በዓለም አደባባይ ማኩራት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያዊነትን መልሕቅ አበርትተን መያዝ ይኖርብናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
