“ሀገርን ከጥቃት መከላከል የኩራት ሁሉ ምንጭ ነው” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

7
ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 130ኛው የዓድዋ ድል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። በክብረ በዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ መላውን ጥቁር ያኮራ፣ ጭቁን ሕዝቦችን ለነጻነት ትግል ያነቃቃ መኾኑን ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል ባርነትን በመጠየፍ፣ በባዕድ ላለመገዛት፣ ሉዓላዊነትን እና ነጻነትን ላለማስነካት፣ በጀግንነት፣ በአይበገሬነት እና በአንድነት ቆመው በመዋጋት፣ ቅኝ ገዢዎችን አሸንፈው ሀገራቸውን ያዳኑበት የጸረ ቅኝ ግዛት ድል የተመዘገበት መኾኑን ገልጸዋል።
የቅኝ ግዛት ቀንበር ከጥቁር ሕዝቦች ጫንቃ ላይ እንዲወገድ መንገድ የተከፈተ የተጋድሎ ታሪክ ነው ብለዋል። ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ መሥራት የማይችሉ ናቸው የሚለውን የፋሽስት አስተሳሰብ የሰበረ ቀንም ነው።
ኢትዮጵያውያን በጦር እና በጋሻቸው፣ በአይበገሬት ወኔያቸው ጠላትን ያሳፈሩበት መኾኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያን ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት ያዳኑበት የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል መኾኑን ገልጸዋል። በዓድዋ ላይ የተሸነፈው ቅኝ ገዢ መርዝ የጫኑ አውሮፕላኖችን ይዞ ዳግም መምጣቱን አስታውሰዋል። አርበኞቻችን ግን በጀግንነት ሀገራቸውን ከጠላት ማዳናቸውን አንስተዋል።
የኢጣልያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው፤ በዓድዋ ድል የተሸነፈው የኢጣልያ ፋሽስት ገዢ መደብ እንጂ የኢጣልያ ሕዝብ አይደለም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ጀግኖች የማይበገሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
አርበኝነት፣ ጀግንነት እና በራስ መተማመን ከዓድዋ በፊት የነበረ፣ በዓድዋ ድል የተደገመ፣ እስከዛሬ ያለ ታሪካችን ነው ብለዋል። ጀግኖች በደማቸው እና በአጥንታቸው ሀገር ያስከበሩ ወላጆቻችን ናቸው፤ እኛም የእነርሱን ታሪክ በመውረስ ሀገር ለማስቀጠል እየሠራን ያለን የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ነን ነው ያሉት።
ከአርበኝነት ባሻገር ለጠላት ያደሩ ባንዳዎች እንደነበሩም አንስተዋል። የዓደዋ ድል ሕዝባችንን ብቻ ሳይኾን ባንዳዎችንም ነጻ ያወጣ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ የባንዳዎችን ክህደት እየነገርን ባንዳን የሚጠየፍ እና አርበኛን የሚወድ ትውልድ መፍጠር አለብን ነው ያሉት። የባንዳነት ታሪክ ካልተወገዘ አርበኛን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያስቸግር ተናግረዋል።
በጋራ የቆሙ ጀግኖች እንደነበሩ ሁሉ ከጠላት ጋር የቆመ ባንዳም ነበር፤ አሁንም የባንዳ ርዝራዥ ኢትዮጵያን ለመሸጥ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚሠሩ የዘመኑ ባንዳዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ግን ባንዳዎችን እየመከተ መኾኑን ገልጸዋል። የሀገር ምሽግ እና የሉዓላዊነት አጥር የኾነውን መከላከያ ሠራዊት የሚወጋ ባንዳ እንጂ ታጋይ ሊኾን አይችልም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪካዊ እና በወቅታዊ ጠላት ድብቅ አላማ ሀገሩ እንዳትጎዳ ማድረግ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
ሀገርን ከጥቃት መከላከል የኩራት ሁሉ ምንጭ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ በአንድነት መቆም እና በሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረን ጥቃት መመከት አርበኝነት ነው ብለዋል። እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነን ነው ያሉት።
ታዝሎ የሚመጠውን የውጭ ጠላት እና አዝሎ የሚመጣውን የእኛን ባንዳ በእኩል እንዋጋለን ብለዋል። ባንዳን አሸንፈን ሀገራችንን እናስቀጥላለን ነው ያሉት። በአንድነት ስንቆም ጠላት አይመጣም ብለዋል።
የዓድዋ ጀግኖችን ታሪክ የወረሰው ጀግናው የሀገር መከለካያ ሠራዊት ሀገሩን እየጠበቀ ለትውልድ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። ዓድዋ የመላው ሕዝብ ኩራት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የጥንካሬ ማሳያ ገድል ነው ብለዋል።
የቤታችንን አመል መምራት እና መግራት ተስኖን ለጠላቶቻችን ክፍተት መፍጠር የለብንም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ከፍታ አይቀሬ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
Next article“የባሕር በር የማግኘት መብታችን የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ