ዓድዋ ዓለም የአሸናፊዎች መኾኗን አሳይቷል።

7
ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የነገሡ መንግሥታት ግዛታቸውን ወደ አፍሪካ ሲያስፋፉ ኢትዮጵያንም ለማስገበር ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። የጥንቷ ሮማ ወይንም የአሁኗ ጣሊያን ደግሞ በቀዳሚነት ትቀመጣለች።
አውጉስቶስ ቄሳር እና ኔሮ የተባሉ የሮማ ነገሥታቶች ጦራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው ድል ተመትተው መመለሳቸውን ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ አስቀምጠውታል።
ጣሊያኖች በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ከቀይ ባሕር፣ ሕንድ ውቅያኖስ እስከ ዛንዚባር ያለውን አካባቢ ለመቆጣጠር በሃይማኖት ሰበብ በ1862 ዓ.ም በአባ ጁሴፔ ሳፔቶ አማካይነት ወደ አሰብ ገቡ። ከአካባቢው ባላባቶች በገዙት ቦታ ላይ “ሩባቲኖ” የሚባል የመርከብ ኩባንያ በአሰብ ወደብ እንዲመሠርትም አደረጉ።
በ1874 ዓ.ም ደግሞ የጣሊያን መንግሥት ወደቡን ተረክቦ የግዛቱ አካል መኾኑን አወጀ። በምጽዋም ጦር በማስፈር ወደ መሀል ኢትዮጵያ መስፋፋቱን ቀጠለ። በሁለቱ ሀገራት መካከል መካረሩ እየጠነከረ ሂዶ ዶጋሌ ላይ በተደረገ ጦርነት ድል ተመቱ።
ጣሊያን ርቀት ላይ ያለን ቦታ መምታት የሚችል 52 “የተራራ መድፎችን” እና የታጠቀ 20 ሺህ ዘመናዊ ሠራዊት አሰልፋ በ1888 ዓ.ም በድጋሜ ወረራ ፈጸመች። በኢትዮጵያ በኩል 42 መድፎች ያሉት፣ ከኢጣሊያ ሠራዊት ከአምስት እጥፍ የሚበልጥ ትጥቅ እና ስንቅ በራሱ የኾነ የገበሬ ጦር የጠላትን ጦር መፋለም ጀመረ። ሰዓታትን በወሰደው እልህ አስጨራሽ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ተደመደመ። በጦርነቱ በኢትዮጵያ በኩል ብዙዎች ቆሰሉ፤ በርካቶች ደግሞ ሕይዎታቸውን አጥተዋል።
በኢጣሊያ በኩል ደግሞ ጄኔራል አሪሞንዲ እና ዳቦር ሜዳ ዓድዋ ላይ ሕይዎታቸው ሲያልፍ የኋላ ደጀን የነበረው ጄኔራል ኤለና ወደ ኋላ ሸሽቷል። ጀኔራል አልቤርቶኒ እና በርካታ መኮንኖችም ተማርከው አዲስ አበባ ከቆዩ በኋላ በሁለቱ ሀገራት ሥምምነት መሠረት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል የታሪክ መምህር መሠረት ወርቁ በአማካይ ስድስት ሰዓት በማይሞላ ደም አፋሳሽ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን ድል ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
በወቅቱ በተፈጠረው ሀገራዊ አንድነት ሕዝቡ ያለምንም የሃይማኖት፣ የጎሳ፣ የጾታ ልዩነት በጦርነቱ መዝመት መቻሉ፣ የመሪዎቹ የመሪነት ጥበብ እና የዲፕሎማሲ አቅም ደግሞ ለድሉ በምክንያትነት አንስተዋል። ጦርነቱ ከመደረጉ በፊት በትጥቅ፣ በስንቅ፣ በሥነ ልቦና፣ በጊዜ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ እና አብዛኛው ሕዝብ ከግብርና ሥራ ነጻ ኾኖ ወደ ጦርነት የሚዘምትበት ተስማሚ ጊዜ መምረጥ መቻሉ፣ በሥነ ልቦናቸው ጠንካራ፣ በሙያቸው እና በሥነ ምግባራቸው ጥንቁቅ የኾኑ የጦር መሪዎች ጦሩን እንዲመሩት መደረጉ ለድሉ ሌላው ምክንያት ነበር ብለዋል።
የመልካዓ ምድራዊ አቀማመጡ ለጠላት ባዕዳ መኾኑ፣ የኢትዮጵያ ሰላዮች የማሳሳት አቅም፣ የኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነት፣ አይበገሬነት፣ ወኔ እና ጀግንነት በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመን መፈጠሩ ሌላው ምክንያት ነው።
የጣሊያን ጦር የኢትዮጵያን የጦር አቅም አሳንሶ ማየቱ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት የተከፋፈለ፣ ከንጉሡ ጋር ያለመግባባቶች እንዳሉ አድርጎ መረዳቱ እንዲሁም ጦሩ የተሰላቸ፣ የሎጀስቲክስ ችግር እንዳጋጠመው በማመኑ ዓድዋ ላይ ድል ለመደረጉ ይነሳል።
መምህሩ እንዳሉት የዓድዋ ድል ብሔራዊ ኩራትን፣ አንድነት እና አብሮነትን አጎልብቷል። የውጫሌ ሥምምነት እንዲሰረዝ አድርጓል። የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት እንዲጎለብት አድርጓል። ዓድዋ ዓለም የአሸናፊዎች መኾኗን አሳይቷልም ብለዋል።
ከፍትሕ ጋር የቆሙ ጣሊያኖች እና ሌሎች ሀገራት ዜጎችም ተፈጥረዋል። “ነጮችን የበላይ፣ ጥቁሮችን የበታች” አድርጎ የማየት እሳቤ እንዲሰበር፣ የእኩልነት ንቅናቄ እንዲፈጠር አድርጓል። ዓድዋ በርሊን ላይ የተደረሰውን የቅኝ ግዛት ውል የሰበረ ነው።
በዓለም ላይ የሚገኙ ጥቁሮች ከባርነት ለመላቀቅ፣ ለእኩልነት እና ለፍትሕ እንዲታገሉ በር ከፍቷል። በቅኝ ግዛት የሚገኙ ሀገራት ለነጻነት፣ ከነጻነት በኋላም ሀገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለሙን በመቀያየር አርማቸው አድርገው እንዲጠቀሙ አድርጓል ብለዋል።
ለጋራ ዓላማ በአንድነት መሰለፍ ከተቻለ የማይቻል ነገር እንደሌለ፣ ብልህ እና ቆራጥ አመራር ለታላቅ ድል እንደሚያበቃ የዓድዋ ድል ለአሁኑ ትውልድ ትልቁ ትምህርት ይሰጣል።
በሃይማኖት፣ በዘር ወይም በፖለቲካ ልዩነት ሳይከፋፈል በአንድነት መሰለፍ ከተቻለ የቱንም ያህል ኀያል የኾነን ጠላት ማሸነፍ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው።
ዘጋቢ፦ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኪነ ጥበብ ለዓድዋ
Next articleየዓድዋ ድል ሚስጢሩ የኢትዮጵያውያን የዓላማ ጽናት እና የሀገር ፍቅር ነው።