
ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነት የተገመደበት የደም ቃል ኪዳን ነው። ኢትዮጵያውያን ዕድሜ፣ ጾታ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የሥራ ዘርፍ እና ሌሎች ጉዳዮች ሳይገድቧቸው በአንድነት እና በጽናት ተሳትፈው ድል ተቀዳጅተውበታል።
በዚህም ታሪክን በደማቅ ቀለም ጽፈው ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ተምሳሌት ኹነዋል። ኪነጥበብ ደግሞ ለዓድዋ ጀግኖች አይተኬ ሚና ነበረው።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ድኤታ አርቲስት ነብዩ ባዬ ኪነጥበብ በዓድዋ ድል ታሪክ ባሕላዊ እና ዘመናዊ በኾነ መንገድ ሰፊ አበርክቶ እንደነበረው ተናግረዋል።
በቀደመው ጊዜ በዓድዋ ዘመቻ እና ድል ታሪክ ውስጥ ስነቃሎች፣ ተረቶች፣ አባባሎች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ባሕላዊ ዜማዎች፣ ኾታ፣ ቀረርቶ፣ ፍከራ እና ሽለላ በባሕላዊ መንገድ የዓድዋ ጀግኖችን በማበረታት እና በማጀገን ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ነው ያነሱት።
ስለ ሀገር እና ወገን ምንነት፣ ጀግንነት፣ ሉዓላዊነት እና መሰል ጉዳዮችን በትውልዱ አዕምሮ ላይ ከታች ጀምሮ የሚስል ነው ብለዋል። በአዕምሮ ላይ የተሳለ የሀገር ስዕል ደግሞ ሀገር ተደፈረች በሚባልበት ጊዜ ብድግ ብሎ የሚነሳ መኾኑንም አንስተዋል። በዓድዋ ዘመቻ እና ጦርነት የኾነውም ይህ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያውያን ወደ ዓድዋ ዘመቻ በሚተሙበት ጊዜ እንደእነ አዝማሪ ጻድቄ ያሉ አዝማሪዎችን ጨምሮ ብዙ ቁጥር ያላቸው አዝማሪዎች ሀገሬውን በዜማ በማበረታት ረገድ ከፊት ተሠልፈው ከፍተኛ ሚና እንደተወጡ ጠቅሰዋል።
ከድል በኋላ ደግሞ ዘመናዊው የኪነጥበብ መንገድ ደማቁን የዓድዋ ድል ቀርጾ በማስቀመጥ፣ አሁን ላይ ያለው ትውልድ እንዲያውቅ በማድረግ እና ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ በኩል ሰፊ አበርክቶ እንዳለው ነው የተናገሩት። የኪነጥበብ ሰዎች ድርሰት፣ ግጥም፣ ተውኔት፣ ፊልም፣ ሙዚቃ እና የመሳሰሉትን ሥራዎች በመሥራት ታሪክን ለትውልድ ለማቀበል ጥረት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላቸው የተለያዩ የኪነጥበብ ሙያተኞች መካከል ፀጋየ ገብረመድህን፣ ፕሮፌሰር ኀይሌ ገሪማ፣ አባተ መኩሪያ፣ እጅጋየሁ ሺባባው፣ ቴወድሮስ ካሳሁን እና ሌሎችም የሠሯቸው ሥራዎችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኪነጥበብ ሰው ሀገር የሚሠራ እና ሀገርን የሚስል የሀገር ፍቅር ያለው፣ የሀገር ችግር የሚገባው፣ የሀገር ድል የሚያስደስተው፣ የሀገርን ደስታ ሌሎች ሀገሮች እንዲጋሩ እና ችግሯን ቀድመው እንዲመለከቱላት የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በጣሊያን ወረራ ጊዜ የሀገር ሉዓላዊነት መደፈር ቀጥታ የሚመጣበት እና ኪነጥበብም እሱን ያሳየበት ኹኔታ ነበር ያሉት ሚኒስትር ድኤታ አርቲስት ነብዩ ባየ አሁን ላይ ግን የሀገር ሉዓላዊነትን የመዳፈር ኹኔታ በእጅ አዙር የሚመጣበት አጋጣሚ እንዳለ ነው የተናገሩት። ለአብነትም በኪነጥበብ (በሙዚቃ፣ በፊልም፣…) እና በባሕል ወረራ ተጀምሮ ኢኮኖሚ ወደ ማሳጣት እና ቅኝ ወደ መግዛት እንደሚሸጋገር አንስተዋል።
ይህን ደግሞ የኪነጥበብ ሰዎች ቀደም ሲል ኢትዮጵያውያንን በኪነጥበብ አነሳስተው ዓድዋ ላይ ለድል እንዳበቁ ሁሉ አሁንም ትውልዱን በኪነጥበብ በማነሳሳት የኢኮኖሚ፣ የሀሳብ፣ የባሕል ሉዓላዊነት እና ሀገርን ትልቅ የማድረግ ሥራዎች ላይ ሊያግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
