
አዲስ አበባ፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ፒያሳ በሚገኘው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የጦር መኮንኖች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።
የዘንድሮው በዓል “ዓድዋ 130፤ ከአኩሪ ታሪክ፣ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር የአባቶቻችንን ጀግንነት በማስታወስ ብቻ ሳይኾን፣ ለሀገራችን ሰላም እና ዕድገት በጋራ ለመቆም ቃል በመግባት መኾን ይኖርበታል ብለዋል።
ጀግንነት ማለት በጦር ግንባር ብቻ ድል ማስመዝገብ ሳይኾን፣ ልዩነቶችን በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ድህነትን እና ኋላ ቀርነትን ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማስወገድ መኾኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እና ሌሎች የስኬት ሥራዎች የ”ዳግማዊ ዓድዋ ድል” ውጤቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የታላቁ የዓድዋ ድል ቀጥተኛ ወራሽ መኾኑን ገልጸዋል።
ሠራዊታችን የዓድዋን መንፈስ በልቡ ሰንቆ እና የአርበኞች አባቶቹን ፈለግ ተከትሎ፣ የሀገሩን ሉዓላዊነት እና የሕዝቡን ደኅንነት ሌት ተቀን እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዓድዋ ያስተማረን ትልቁ ቁምነገር ለአንድነት እና ለሀገር ጥቅም መቆም የማይደራደሩባቸው የህልውና ጉዳዮች መኾናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ሠራዊቱ ይህንን ጽኑ መሠረት በመያዝ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶ ኾኖ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢንጅነር አይሻ አክለውም የአባቶቻችንን የጀግንነት ታሪክ አሁን ካለው የብልጽግና ጉዞ ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በጠንካራ መከላከያ ተቋም ግንባታ ከፍ ማድረግ “ለዳግማዊ ዓድዋ ድል” መሠረት መኾኑን አስገንዝበዋል።
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ከሕዝቡ በሚያገኘው ድጋፍ ታጅቦ የዓድዋን አደራ ለመጠበቅ እና ሰላምን ለማረጋገጥ ምንጊዜም ዝግጁ መኾኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
