‎ከዓድዋ ድል ወጣቶች ምን ይማራሉ?

2
‎ባሕር ዳር: የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የዓድዋ ድል በሕዝቦች ደም የተጻፈ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ነው።
ድሉ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ጽኑ መሠረት ከመኾኑም በላይ ለወጣቱ ትውልድ በርካታ ተግባራዊ ትምህርቶችን የሚሰጥ የታሪክ አሻራም ነው። በየዓመቱ የካቲት 23 የሚከበረው ይህ ታላቅ ድል በጀግኖች አያቶቻችን ደም እና አጥንት የተጻፈ የነጻነት እና የአይበገሬነት ምልክትም ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ለመኾኑ ወጣቶች ይህንን ታሪክ ምን ያህል ያውቁታል? ከዓድዋ ድል ታሪክስ ምን ይማራሉ?
‎በዚህ ዙሪያ ከአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረገችው ወጣት ሜልኮን ጌትነት የዓድዋ ድል በደም ታሪክ የተጻፈ የኢትዮጵያውያን ገድል ነው ብላለች። ዓድዋ ለሌላው ዓለም ትምህርት የኾነ ታላቅ ገድል እና የኢትዮጵያውያን ማንነት የሚታይበት መስታወት መኾኑንም ገልጻለች።
‎ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫ እና በዲጅታል ዓለም ለሚፈጠሩ ጫናዎች እንደ “መልሕቅ” የሚያገለግል ታሪክ እንደኾነም አንስታለች።
‎ድሉ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ኢትዮጵያዊ ብሂል በተግባር የታየበት እና ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ባንዲራ ስር በመሰብሰብ የተፈጸመ ታላቅ ታሪክ እንደኾነ ነው የገለጸችው።
‎በዓድዋ ድል የሴቶች ሚና በእቴጌ ጣይቱ የጦርነቱ “የንጉሱ የፖለቲካ አዕምሮ” እንደነበሩ አንስታለች። እቴጌ ጣይቱ የፖለቲካ እና የጦር አመራር ብቃት፣ እንዲሁም የሌሎች ሴቶች ተሳትፎ የሀገሪቱን የቀደመ ዘመናዊ አስተሳሰብን የሚያሳይ እንደነበር ጠቁማለች። ድሉ የሰው ልጅ በሰውነቱ እንዲከበር መሠረት በመጣሉ ለጥቁር ሕዝቦች እና ለመላው ዓለም የነጻነት ተምሳሌት መኾኑን ተናግራለች።
‎ታሪክ የሌለው ሰው ስር እንደሌለው ዛፍ መኾኑን በመጠቆም ወጣቶች ከዓድዋ ድል ታሪክ በመማር በዲጂታሉ ዓለም ማንነታቸውን ጠብቀው ሊጓዙ ይገባል ነው ያለችው።
‎ወጣቶች ወቅታዊውን ድህነትን፣ ድንቁርናን እና መለያየትን ለማሸነፍ የዓድዋን የአንድነት መንፈስ በሚሠማሩበት የሙያ ዘርፍ ሁሉ በመድገም ራሳቸውን ከድህነት ነጻ ለማውጣት መትጋት እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳቧን ለግሳለች።
‎ሌላው ሀሳቡን ያካፈለን ወጣትም ዓድዋ ለሀገር ክብር እና ለነጻነት ሲባል የዘር፣ ሃይማኖት እና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በጋራ የተሳተፈበት ጦርነት እንደኾነ ገልጾልናል።
‎ዓድዋ እርስ በእርስ መከባበርን እና የመሪነት ጥበብን ያስተምራል ነው ያለው። እቴጌ ጣይቱ በጦርነቱ ሴትነት ሳይበግራቸው ትልቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል። ኢትዮጵያ ጣሊያንን ማሸነፏ ጥቁር አያሸንፍም የሚሉትን አውሮፓውያንን አንገት ያስደፋ መኾኑንም አንስቷል።
‎ከዓድዋ ወጣቱ ጽናትን፣ ለሀገር በአንድነት መቆምን፣ መሪን ማክበርን፣ በማንነት መኩራትን ይማራል ነው ያለው። አሁን ላይም ወጣቶች የጀግኖች ዘር መኾናቸውን መርሳት የለባቸውም፤ አያቶቻችን የተዋደቁለትን ዓላማ በማሰብም ከታሪክ መማር እንደሚገባ ተናግሯል።
‎ነጻ ሀገር ያስረከቡን አያቶቻችንን የጥንካሬ መንፈስ እና ስለ ሀገር ያላቸውን ጽናት ማስቀጠል እንደሚገባም ነው የገለጸው።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዓድዋ የኢትዮጵያ አንድነት የተጠናከረበት ታሪካዊ መሠረት ነው።
Next article“ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የታላቁ የዓድዋ ድል ቀጥተኛ ወራሽ ነው” ኢንጅነር አይሻ መሐመድ