
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር በር የሀገራትን ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ አቅም ለመገንባት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል። ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፉክክር እያየለ በመጣበት በዚህ ዘመን ኀያላን ሀገራት ከድንበራቸው ብዙ ርቀትን ተሻግረው በባሕር ዳርቻዎች ዙሪያ ጦራቸውን እያሠፈሩ እና ተጠቃሚነታቸውን እያሰፉ ይገኛሉ።
በአፍሪካም የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሲተጉ ይስተዋላል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ደግሞ የባሕር በር ተቆልፎባቸው ይገኛል።
በታሪክ በተከሰቱ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ ከእጆቿ የነበሩ የባሕር በሮች መውጣት ዛሬ ላይ የበይ ተመልካች እንድትኾን አድርጓታል።
የደፕሎመንት ኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ገመችስ መርሻ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለዘመናት የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች አንስተዋል። አሰብን ጨምሮ ሌሎች ወደቦች እንደነበራት አንስተዋል።
የባሕር በሯን ተጠቅማ ደኅንነቷን የማስጠበቅ፣ የውጭ ግንኙነቷን የማሳለጥ፣ ከባሕር የሚገኙ ገጸ በረከቶችን የመጠቀም እና ያለ ወደብ ክፍያ ግብዓቶችን የማጓጓዝ ተጠቃሚነት እንደነበራት ተናግረዋል።
ወደ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ወደ አውሮፖ እና ኢንዶኔዥያ የምታደርጋቸው የንግድ እና የውጭ ግንኙነቶች፣ የአሕጉሯን ደኅንነት ለማስጠበቅ የምታከናውናቸው ተግባራት ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ወሳኝ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
በታሪክ አጋጣሚ የባሕር በር ማጣቷ እና በጅቡቲ ወደብ ብቻ መጠቀሟ በኢኮኖሚ ዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትን ዋቢ በማድረግ ከ19 እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የወደብ ኪራይ እንደምትከፍል አንስተዋል። ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ገንዘብ አሁን ላይ እየተሠሩ የሚገኙ የጉባ ብሥራት ፕሮጀክቶችን እንደ ኑክሊየር ኀይል እና የማዳበሪያ ፋብሪካ መሰል ፕሮጀክቶችን ወጭ የሚሸፍን መኾኑን ተናግረዋል።
የባሕር በርን በማጣታችን ወደ ውጭ በሚላኩ እና በሚገቡ ምርቶች ላይ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ፣ የኑሮ ውድነትን በማስከተል፣ ምርቶች በጉዞ ላይ የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዲያልፍ በማድረግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ተመራማሪው ጠቁመዋል።
የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገሪቱ ለልማት እንዳይገቡ፣ የሥራ እድል እንዳይፈጠር፣ ከባሕር የሚገኙ ማዕድናት፣ የዓሳ ምርት እንዳትጠቀም በማድረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው ብለዋል።
የባሕር በር ማግኘት የሀገሪቱን እድገት 35 በመቶ የሚጨምር መኾኑን ተናግረዋል። ምርቶች በወቅቱ እንዲመጡ፣ የሥራ እድል እንዲፈጠር፣ የውጭ ኢንቨስትመንቶች እንዲመጡ፣ የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ፣ የሀገሪቱ የባሕር ኀይል ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ የባሕር ማዕድናትን እንድትጠቀም፣ የቱሪዝም ተደራሽነቷ እንዲያድግ የባሕር በር የማግኘት ትሩፋቶች ናቸው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተቀብሎታል ነው ያሉት። ባሕር በር ማግኘቷም ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለው ዓለም አምኖበታል ነው ያሉት።
ታሪኩን የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጣዊ አንድነቱን በማጠናከር፣ ለሀገር ዕድገት እና ደኅንነትን የሚያሰጠብቅለትን የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል። በሀገር ጥቅም ላይ አንድ መኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
