
አዲስ አበባ፡ የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም እና የጸጥታ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ምክክሩ “ሰላማዊ ፖለቲካ ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ ያለው።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ የሰላም ሚኒስቴር ከተሰጡት ተልዕኮዎች ዘላቂ ሰላም በሀገሪቱ እንዲሰፍን ማስቻል መኾኑን ገልጸዋል። ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የጸጥታ ሥራ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ቁርሾን መሠረት ያላደረገ አካሄድን እየተከተለ መኾኑን ገልጸዋል። የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው የቆዩ አካላት የሰላም አማራጭን ከተቀበሉ መንግሥት በሩ ክፍት እንደኾነም ተናግረዋል።
ሥልጠና በመስጠትም ሰላማዊ ሂደትን እንዲከተሉ እና መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ እየሠራ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተካሄደው ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የጸጥታ ሥራ የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር አስችሏል ያሉት ሚኒስትሩ ልምዱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የሰላም ተዋናዮችን ማሳተፍ እና ተግባራትን በአግባቡ መፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል።
አብሮነትን ማሳደግ የሕዝብን እሴት መጠበቅ እና የሕዝብን የእርስ በእርስ መስተጋብር በማዳበር ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
