የማጅራት ገትር መንስኤ እና መፍትሄው!

10
‎‎ባሕር ዳር: የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የበጋ ወቅት ሙቀትን ተከትሎ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል የማጅራት ገትር ወይም ሜኒንጃይትስ በሽታ አንዱ ነው፡፡
‎በድሪም ኬር ትሬዲንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስት ሀኪም እና አማካሪ የኾኑት ዶክተር መኮንን አይችሉህም የማጅራት ገትር በሽታ በቫይረስ፣ በባክቴሪያ፣ በፈንገስ እና በፓራሳይት ሊነሳ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በበጋ ወቅት የሚከሰተው እና ተላላፊ የኾነው በባክቴሪያ የሚነሳው የማጅራት ገትር በሽታ ነው ብለዋል፡፡ ሜኒንጆፎካል ሜኒንጃይተስ በሚባል የባክቴሪያ አይነት በሽታው እንደሚከሰትም ነው የገለጹት፡፡
‎አንጎልን የሚሸፍኑት ሦስት ሽፋኖች ሜኒንጅስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ አካላት ላይ ብግነት የሚያስከትል በመኾኑ ነው ሜኒናጃይትስ የተባለው ብለዋል፡፡
‎በሽታው ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ አማኝነት የሚተላለፍ ሲኾን በፍጥነት የሚተላለፍ እና ለሞት የሚዳርግ ጭምርም እንደኾነ ገልጸዋል።
‎ሜኒንጃይት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ እና ምዕራብ አፍሪካ ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ የሚያጠቃ በሽታ ነው ብለዋል፡፡
‎በሽታው በወቅቱ ተገቢ ሕክምና ካለተደረገለት በስተቀር በፍጥነት እየተዛመተ ሰዎችን የሚያጠቃ እንደኾነም ገልጸዋል።
የበሽታው ምልክቶችም፦
👉 የላይኛው የመተንፈሻ አካል ችግሮች
👉 የዓይን መቅላት
👉 ከፍተኛ ትኩሳት
👉 ከፍተኛ ራስ ምታት እና አንገትን ወደ ኋላ በመቆልመም ማጅራትን መያዝ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።
በሽታው በጣም ሲጠና ደም የቋጠረ ሽፍታ በሰውነተ ላይ ይከሰታል፤ ይህም የበሽታውን መጠንከር የሚያሳይ መጥፎ ምልክት እንደኾነም አብራርተዋል።
‎የአካል ምርመራ ሲደረግ አንገትን ወደ ደረት ለመመለስ መቸገር እና የአንገት መግረር ያሳያል ነው ያሉት፡፡
‎እነዚህ ምልክቶች ሲከሰቱ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም በመሔድ የአካል እና የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በሽታው የተገኘበት ሰው በሚኖርበት አካባቢ ያሉ ሰዎች ላይ ቅኝት በማድረግ እና ሰው የሚበዛባቸውን አካባቢዎች ትምህርት ቤት፣ ወታደራዊ ካምፕ እና ስደተኞች ያሉበት አካባቢ የወረርሽኝ ምላሽ ሰጭ ክትባት እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡
‎በሽታውን ለመከላከል ምልክቶች ሲታዩ ፈጥኖ ወደ ሕክምና መሄድ፣ አፍ እና አፍንጫን በመሸፈን ወደ ሌላ እንዳይተላለፍ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
ማጅራት ገትር በሽታ በወቅቱ ካልታከመ የጀሮ አለመስማት፣ ዓይነ ሥውርነትን፣ የሚያንቀጠቅጡ እና የሚጥሉ ችግሮችን ብሎም ሞትን እንደሚያስከትል ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ በቁጭት መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር ተወያዩ።