
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንዲት ሀገር ሉዓላዊነቷን ለማስከበር፣ የሕዝቦቿን ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ዕድገቷን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የተለያዩ ተግባራትን ታከናውናለች።
ይህም በዋነኝነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ለመቅረጽ እና ከሀገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለመወሰን እንደ መሠረት ያገለግላል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል የታሪክ መምህር ሙሉጌታ ያለው ብሔራዊ ጥቅምን አስመልክቶ ከአሚኮ ዲጅታል ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ብሔራዊ ጥቅሞች አንዲት ሀገር ሉዓላዊነቷን፣ ኢኮኖሚያዊ ደኅንነቷን፣ ዕድገቷን፣ ባሕላዊ እሴቷን እና ሌሎች ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ናቸው ብላ የምትወስዳቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ብሔራዊ ጥቅሞቿን እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ መሥራቷን ያነሱት መምህር ሙሉጌታ ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ዓድዋ አንዱ ማሳያ መኾኑን ጠቁመዋል።
ሉዓላዊነት ብሔራዊ ጥቅም መኾኑንም አንስተዋል። በዓድዋ ታሪክ መከፋፈል እና ልዩነትን በማስቀረት አንድነትን ማስጠበቅ ተችሏል ነው ያሉት።
ከዓድዋ ድል በኃላ ከውጭ ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት መጠናከር፣ በአዲስ አበባ የኢጣሊያ ኢምባሲን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ኢምባሲዎች መከፈት እና ለኢትዮጵያ ዓለማቀፋዊ ዕውቅና መሰጠት ከድሉ በኋላ የተገኙ ብሔራዊ ጥቅሞች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ በመሠረተ ልማቶች፣ በኀይል አማራጮች፣ በቴሌኮም፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት እና ሀገር በቀል ምጣኔ ሀብትን በማሻሻል ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ እየሠራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
የውጭ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሀብት ትብብርን በመፍጠር፣ በምሥራቅ አፍሪካ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ በመሠማራት፣ በሕዳሴ ግድብ ላይ ድርድር በማድረግ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመቆጣጠር እና ወደ ሀገሪቷ እንዳይገቡ ትግል በማድረግ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር እየሠራች መኾኑን መምህር ሙሉጌታ ተናግረዋል።
በቀጣይ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት አስፈላጊ መኾናቸውን አንስተዋል። ብሔራዊ ጥቅም በውስጥ ብሔራዊ መግባባት እና በውጭ ዘላቂ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሠረተ መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የውስጥ አንድነት እና ዘላቂ ሰላምን በመገንባት፣ የጋራ ታሪክ እንዲጸባረቅ በማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ ዘላቂ የኾነ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድልን በመፍጠር እንዲሁም ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት በማድረግ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዓለማቀፋዊ መድረኮች ላይ ተሳታፊ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ በመኾን ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ እንደሚቻልም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
