
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መሥተዳድር ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ሥብሠባውን አካሂዷል።
መሥተዳድር ምክር ቤቱ ባካሄደው በመደበኛ ሥብሠባው የሰላም አማራጭን ተቀብለው የተመለሱ እና በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ስር ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞው የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መንግሥት ሥራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አሳልፏል።
የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማጽናት እና ልማትን ለማረጋገጥ ባለው ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።
በመንግሥት የሰላም ጥሪ፣ በድርድር እና በውይይት የሰላም አማራጭን ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ የቀድሞው የመንግሥት ሠራተኞች ወደ መንግሥት ሥራቸው እንዲመለሱ የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ወስኗል።
ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቀጣይም ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በመፍታት ለሰላም እና ዕድገት መረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
