ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት ይሠራል።

5
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት የምርጫ ማኒፌስቶ እና ምልክት ትውውቅ አካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን ቃል የገባነውን እና የተሰጠንን እድል በመጠቀም ሀገርን ለማሳደግ ሠርተናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም እና በልማት ተምሳሌት እንድትኾን በመሠራቱ የሚታይ ለውጥን ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።
የባሕር በር ማንሳት እንደ ጥፋተኛ የሚቆጠርበትን ሴራ በማስቀረት ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት የሚያስችል ተግባር እያከናወነ መኾኑን አንስተዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በኮሪደር እንድትለማ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች የልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ፣ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትኾን ተሠርቷል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ፓርቲው በሰላም፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ለመኾን እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ፓርቲው ያመጣው ለውጥ የሀገርን ስብራቶች የለየ፣ መፍትሔ የሚኾኑ አማራጮችን የተገነዘበ፣ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ የሚያደርሳትን ጉዞ ያስጀመረ እና ያስቀጠለ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል የሚያስችል የብሔራዊ ትርክት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በመሪዎች ግንባር ቀደም ተሳትፎ እየተጠናቀቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሀገርን ሉዓላዊነት የምናስቀጥል መኾናችንን የምናሳይበት፣ የኢትዮጵያን ያልተቋጨ ችግሮችን የምንፈታበት፣ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶችን የምናስቀጥልበት፣ የኢትዮጵያን የውኃ ሕልውና የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል።
የውስጥም የውጭም ጠላቶች ምርጫው እንዳይሳካ ይሠራሉ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ነገር ግን አይሳካላቸውም ብለዋል።
ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አብራርተዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው።
Next articleምርጫው ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒነት ያለው እንዲኾን በጋራ መሥራት ይገባል።