የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው።

7
ደብረ ብርሃን: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የፓርቲውን የምርጫ ማኒፌስቶ እና ምልክትን የማስተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል።
“ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ የፓርቲው መሪዎች፣ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ጌታቸው ብልጽግና ፓርቲ ውስብስብ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ ወደ ታላቅ ድል የቀየረ ብርቱ ድርጅት መኾኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩ አቶ ሰለሞን በተለይም የብዝኀ ኢኮኖሚ ዘርፎችን በመከተል ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይም በሕዝብ ዘንድ ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ፓርቲ በመኾን ሉዓላዊነቷ የተከበረ እና የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በዲፕሎማሲ መስኮች ያስመዘገባቸውን ስኬቶች የዘረዘሩት አቶ በድሉ እነዚህን ውጤቶች ይበልጥ ለማስቀጠል እና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ የፓርቲው ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት እና ትርጓሜው ለተሳታፊዎች በዝርዝር የቀረበ ሲኾን አባላትም ለምርጫው ስኬታማነት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበመንግሥት የጤና ተቋማት ያለው የመድኃኒት አቅርቦት በቂ ነው ?
Next articleምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት ይሠራል።