የአትላንቲክ ኢኒሼቲቭ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር የመሻት ጉዳይ

11
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ ባሕር በር አልባ የኾኑ ሀገራት የንግድ አስተዋጽኦ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ የቀጨጨ መኾኑ ይነገራል።
እነዚህ ሀገራት በየዓመቱ ከሚያመርቱት ጥቅል ምርት አብዛኛውን ለወደብ ኪራይ ሲያውሉ መውጫ በማጣታቸው የሚደርስባቸው የምርቶች ዋጋ ውድነት ከፍተኛ ነው። በተቃራኒው የባሕር በር ያላቸው ሀገራት በብዙ መንገድ ከፊት የሚቀድሙበት ዕድል እንዳለ ይገለጻል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት ከተፈጥሯዊ መብት እና ከታሪካዊ ባለቤትነት ጋር የሚያያዝ ነው። አሁን ከኢኮኖሚ ፍላጎት ባሻገር የሕልውና ጉዳይ ኾኗል።
ከ3 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ የሳህል ቀጣና ሀገራትን የባሕር በር ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻል ውጥኑ የተጀመረው የአትላንቲክ ኢኒሼቲቭ በአንድ የጎረምሳ እርምጃ በግማሽ ቀን ጉዞ በሚደረስ ርቀት ላይ ጥያቄዋን ላጠናከረችው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥሩ ማስተማሪያ ይኾናል።
አትላንቲክ ኢኒሼቲቭ ቢያንስ አራት ባሕር በር አልባ ሀገራትን የባሕር በር ባለቤት ያደርጋል። እንዴት?
የጉዳዬ መነሻ ሰሜን አፍሪካ ሞሮኮ ነው። ሀገረ ሞሮኮ በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል እንደ ድልድይ ኾና የምታገለግል ናት። የሞሮኮ ደቡባዊ ቀጣና ላይ አጎራባች የኾኑ ሀገራት የባሕር በር የሌላቸው ናቸው። እነዚህ ሀገራት ማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እና ቻድን የሚያጠቃልሉ ናቸው።
በዋናነትም የሳህል ቀጣና እና ማዕከላዊ ሰሀራ ሀገራት ሊባሉ ይችላሉ። በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2023 በንጉሥ ሙሐመድ 5ኛ አሥተዳደር የተወሰነው ይህ ውሳኔ ከቻድ እስከ ሞሮኮ ሰሜን ምዕራብ ጠረፍ ከ3 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚርቅ ቢኾንም የባሕር በር ባለቤት እንዲኾኑ እድል የፈጠረ ነው። ይህም ዳክህላ ወደብ እስከ ቻድ ድረስ በሚዘረጋ የየብስ ኮሪደር ሀገራቱ የወደብ ባለቤት እንዲኾኑ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል። ስያሜውንም አትላንቲክ ኢኒሼቲቭ ብለው ጠርተውታል።
ይህ ኢኒሼቲቭ በቀጣናው መረጋጋት እንዲመጣ እና የኢኮኖሚ ልዕልና እንዲኖር የሚያስችል ይኾናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። በቀጣናው 85 ሚሊዮን ዜጎች ይኖራሉ። ሞሮኮ ከእነዚህ ሀገራት ጋር የሚኖራት የንግድ ልውውጥም በዚያው ልክ ያድጋል።
ለዚህም ይመስላል የተለያዩ ምሁራን ሞሮኮ በዘመናዊ ዓለም የዘመነ ውሳኔ ወሰነች ብለው ያወደሷት። ይህ ተደጋግፎ የማደግን ርዕይ ሰንቆ ወደ ተግባር የተገባው ውሳኔ ሽብርተኝነትን በመከላከል በትምህርት እና በግብርና ዘርፎች የጋራ ለውጥን ለማምጣት ያስችላልም ተብሎለታል።
በእርግጥም በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ላይ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ያደረጉት የሞሮኮ ባለሀብቶች እንደዚህ አይነቱን ውሳኔ ሲሰሙ ለሀገራቸው መንግሥት “አበጀህ” ብለውታል። ከሦስት ዓመታ በኋላ ሙሉ በሙሉ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የዳክህላ ወደብ እና አካባቢው አራቱ የሳህል ቀጣና ሀገራት በቀጥታ ከባሕር ጋር እንዲገናኙ ያስችላል። ለዚህ ደግሞ ከ3 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መገንባትን ይጠይቃል።
✍️ አትላንቲክ ኢኒሼቲቭ የያዘው መልከ ብዙ ጥቅም ሞሮኮ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ እንቅስቃሴ ታሳድጋለች። አራት ሀገራት በቀጥታ ከባሕር ጋር እንዲገናኙ ያስችላቸዋል። ከሰሜን ምዕራብ ሞሮኮ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ማዕከላዊ ቻድ የሚደርስ የግንኙነት መረብ ይዘረጋለታል።
በዚህ ሳያበቃ የቀጣናውን ደኅንነት ከማስጠበቅ እስከ የተቀናጀ የጋራ እድገት ድረስ የሚደርስን ትሩፋት ይዞ መጥቷል። ከናይጀሪያ ወደ ሞሮኮ የሚጓጓዘው 25 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የሚደረግበት የነዳጅ መጓጓዣ ደኅንነቱ እንዲጠበቅም የሚያስችል ነው።
አትላንቲክ ኢኒሼቲቭ ባሕር በር አልባ ሀገራትን የባሕር በር እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ከ3 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የየብስ የመንገድ ኮሪደርን መገንባትን ይጠይቃል። ለዚህም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል። ሀገራቱ ግን በጋራ ለማደግ በመወሰናቸው ፕሮጀክቱን በሞሮኮ ይሁንታ ጀምረውታል።
ኢትዮጵያ ላለፋት አራት አስርት ዓመታት የተጠጋ ጊዜ ከባሕር በር ተገፍታ ቆይታለች። አሁን ደግሞ ወደ ታሪካዊ ይዞታዋ እና ተፈጥሯዊ መብቷ ለመመለስ ጥያቄዋን አጠናክራ ቀጥላለች።
በሌሎች ቀጣናዎች ከ3 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ተጉዞ የባሕር በር እንዲገኝ ሥራዎች ይሠራሉ። ወዲህ ደግሞ በ50 እና 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 130 ሚሊዮን ሕዝብ “የባሕር በር ያለህ” እያለ ለዓለም ሕዝብ ስለ ፍትሕ አቤት ይላል።
በመረጃ ምንጭነት ፍራንስ 24፣ ሲኤን ኤን እና አትላንቲክ ኢኒሼቲቭ ሰነድን በዋቢነት ተጠቅመናል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምርጫውን ነጻ እና ተአማኒ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next articleበመንግሥት የጤና ተቋማት ያለው የመድኃኒት አቅርቦት በቂ ነው ?