
ደብረ ብርሃን: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የፓርቲውን የምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ የማድረጊያ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ፓርቲው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ “ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የስንዴ ነዶ በኾነው የምርጫ ምልክቱ ተፎካካሪ ኾኖ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።
በምርጫው በንቃት መሳተፍ፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ታሪካዊ ኀላፊነትን ለመወጣት በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ፓርቲው በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች የሚከተላቸውን ስልቶች የያዘ ማኒፌስቶ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
ይህም ፓርቲው የተጀመሩ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞዎችን እና ትልሞችን ለማጠናቀቅ ያለውን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት የሚያሳይ እንደኾነ አንስተዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች እና የጥፋት ኃይሎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ትርምስ በመፍጠር ምርጫው እንዳይካሄድ ለማደናቀፍ ጥረት እያደረጉ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት የፓርቲው መሪዎች እና አባላት መሥዋዕትነት ከፍለው ሀገርን እንዳስቀጠሉ ሁሉ አሁንም ትልሟን የምታሳካ ሀገር ለመገንባት ያላቸው ትጋት እንደማይቋረጥ ነው የገለጹት።
የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለማሰናከል ቢሞክሩም ያቀዱት ሕልም የማይሳካ መኾኑን ተናግረዋል። ፓርቲው ቀጣናዊ የኃይል አሰላለፉን በጠበቀ መልኩ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ቁርጠኛ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
