
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂው ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠ ይገኛል። ከቀላል የጥያቄ እና መልስ ልውውጥ አልፈው ራሳቸውን ችለው ተግባራትን የሚያከናውኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ወኪሎች መፈጠር ለዚህ ለውጥ ዋነኛው ማሳያ ነው።
እንደ አይ.ቢ.ኤም ድረ ገጽ መረጃ ከኾነ እነዚህ ወኪሎች የተሰጣቸውን ተግባራት በተናጠል ለማከናወን የራሳቸውን የሥራ ስልት የሚቀይሱ እና በሳይበሩ ዓለም ያሉ የዲጂታል መገልገያዎችን ተጠቅመው ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጡ ሥርዓቶች ናቸው።
ገጹ የእነዚህ ወኪሎች ዋና ሞተር የጎለበቱ የቋንቋ ሞዴሎች መኾናቸውን ገልጾ እነዚህ ሞዴሎች ከተለመዱት የቋንቋ ሞዴሎች በተለየ መልኩ ውጫዊ መረጃዎችን በመፈለግ እና ንዑስ ተግባራትን በመፍጠር ውሥብሥብ ችግሮችን የመፍታት ልዩ አቅም ያላቸው መኾኑን ያስረዳል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወኪሎች የሥራ ብቃት እጅግ የሚደነቅ ኾኗል። አይ.ቢ.ኤም በገጹ እንዳሰፈረው እነዚህ ወኪሎች አንድን ተግባር ለማከናወን የሚረዳቸው ዝርዝር ተግባራትን እና ንዑስ ተግባራትን በራሳቸው የመንደፍ ብቃት አላቸው። በተጨማሪም መረጃ ሲያጥራቸው የድረ ገጽ ማሰሻዎችን በመጠቀም ያሠባሥባሉ።
በጣም የሚገርመው ደግሞ ለእነዚህ ወኪሎች ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ ሞልትቡክ የተሰኘ አዲስ የሶሻል ሚዲያ መድረክ መፈጠሩ ነው፡፡ ይህም የቴክኖሎጂውን ጉዞ ይበልጥ አስደናቂ ያደርገዋል ሲል የገለጸው ደግሞ ዘጋርዲያን ነው።
እነዚህ ወኪሎች በሞልትቡክ ላይ ራሳቸውን ችለው በሚያደርጉት ውይይት በንቃተ ህሊና፣ በሃይማኖት እና በምናባዊ ገንዘብ (ክሪፕቶከረንሲ) ጉዳዮች ትንታኔዎችን እና ክርክሮችን እደሚያደርጉም አክሏል።
ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂው ከመረጃ አቅራቢነት ባለፈ ወደ ማኅበራዊ መስተጋብር ደረጃ መሸጋገሩን ያሳያል። የዘጋርዲያን ዘገባ ሞልትቡክ መጀመሪያ ላይ እንደ ኢሜይል እና ቀጠሮ ማስያዝ ያሉ የተለመዱ እና ቀለል ያሉ ተግባራትን ለሚያከናውኑ ሞልትቦቶች ማሻሻያ ተብሎ የተጀመረ ቢኾንም አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወኪሎች የሚሳተፉበት ሰፊ መድረክ ኾኗል።
ይሁን እንጂ የዚህ ቴክኖሎጂ ዕድገት የራሱ የኾኑ ተግዳሮቶችም አሉት። አይ.ቢ.ኤም እነዚህ ወኪሎች ያገኙትን መረጃ በመተንተን ዕቅዳቸውን በየጊዜው የሚያሻሽሉ እና ካለፉት ግንኙነቶች በመማር ራስገዝ ምላሽ የሚሰጡ ቢኾንም የደኅንነት ጉዳይ ግን አሳሳቢ እንደኾነ ይገልጻል።
ለእነዚህ ወኪሎች የኮምፒውተር እና የኢሜል ሙሉ ፈቃድ መስጠት ለጠላፊዎች ተጋላጭ ስለሚያደርግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ዘጋርዲያን አስረድቷል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወኪሎች በሶፍትዌር ልማት እና የመረጃ ቴክኖሎጂ ሥርዓትን በማዘመን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ አይ.ቢ.ኤም በገጹ አመልክቷል። ሀሳብ የሚጋሩበት ሞልትቡክ የተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጭ ቦቶች እርስ በእርስ በመማማር ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ መድረክ ኾኗል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
