
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ እና 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን ዴሞክራሲን “የሕዝብ፣ በሕዝብ እና ለሕዝብ የሚኾን ሥርዓተ መንግሥት ነው” በማለት ገልጸውታል።
የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንዱ መገለጫ ደግሞ የምርጫ ሥርዓት ነው። በምርጫ ሂደት ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች አለኝ የሚሉትን ሀሳብ ለሕዝብ የሚሸጡበት፣ የፖሊሲ አማራጮችን የሚያቀርቡበት፣ ለመንግሥትነት የሚወዳደሩበትም ነው። በምርጫ ወቅት የሚደረግ ፉክክር የሀገርን ሰላም እና የሕዝብን ደኅንነት ማዕከል ያደረገ ሊኾን እንደሚገባም ምሁራን ያነሳሉ።
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር ካሳሁን አበራ ምርጫ የሚከናወነው በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በመመሥረት ሕዝብን ለማገልገል ነው ብለዋል። ፓርቲዎችም የሚወዳደሩት ሀገርን እና ሕዝብን ለማገልገል መኾኑን ገልጸዋል።
ይህንን ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለምርጫ በሚፎካከሩበት ወቅት ሕዝብን ማስቀደም እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
በምርጫ ለማሸነፍ የሚፎካከሩት ፓርቲዎች ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሀገር አንድነት እና ለሰላም መረጋገጥ ቅድሚያ መሥጠትን ቀዳሚ ጉዳያቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እጩዎቻችም ኾኑ ደጋፊዎቻቸው ተግባቦታቸው በአማራጭ ሃሳቦች እና በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ብቻ መመሥረት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በማንኛውም ሁኔታ በሰከነ እና በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ማስተማር የፖለቲካ ፓርቲዎች ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባም ተናግረዋል።
ፓርቲዎች የሚኖሩት ሕዝብ ሲኖር በመኾኑ በቅስቀሳ ወቅት ሕዝብን ያስቀደመ አካሄድን መከተል እና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
ለምርጫ ቅስቀሳ የሚነሱ ሀሳቦች የተመረጡ እና ኀላፊነት የተሞላባቸው ሊኾኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሕዝቦች መካከል መቃቃርን ከሚፈጥር፣ ግጭት ቀስቃሽ የኾኑ ቃላትን እና ምልክቶችን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባም አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከብሽሽቅ እና ከስሜታዊነት መውጣትን፣ ከጸብ አጫሪነት መራቅን መርህ አደርገው መፎካከር እንደሚኖርባቸው ነው የገለጹት። ኢትዮጵያ ብዝኃ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር እና ባሕል ያለባት በመኾኑ እነዚህን ሁሉ እሴቶች ያከበረ የምርጫ ፉክክር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ስኬታማ የሚኾነውም ዘላቂ የሕዝብ ጥቅምን በማሰብ የተሸናፊነትን እና የአሸናፊነትን ውጤት በጸጋ ለመቀበል የሚያስችል የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል ሲዳብር እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
