ዲፕሎማሲ መልካም ዐይኖች በበጎ እንዲመለከቱ፤ ቅን ልቦች እውነትን እንዲደግፉ ያደርጋል።

5

 

ባሕር ዳር: የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዲፕሎማሲ የዓለም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ከሌሎች ሀገሮች ጋር የሚያደርጉት የመልካም ግንኙነት መሣሪያ ነው። እድገትን፣ ልማትን፣ ሉዓላዊነትን፣ ብሔራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመኾን በውይይት፣ በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ የሚደረግ ወዳጅነት እንደኾነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

እምቢያለ በየነ (ዶ.ር) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምርህ ናቸው። አንድ ሀገር ሉዓላዊ ሀገር ለመባል የባሕር በር ያስፈልገዋል፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ያሉ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ደግሞ የባሕር በር የሕልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው ይላሉ።

ነገር ግን የባሕር በር የሌላት ሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ደኅንነቷን የተጎዳች፣ ብሔራዊ ጥቅሟን የተነፈገች ያደርጋታል ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ድልድይ በሰላማዊ እና በድርድር ዲፕሎማሲ ማካሄድ ነው። በዚህም ወንድማማችነትን እና ወዳጆችን በማብዛት ብሔራዊ ጥቅሟ እንዲከበር ሀገራትም ከጎኗ እንዲቆሙ ያግዛል ነው ያሉት ዶክተር እምቢያለ።

እንደ ዶክተር እምቢያለ ገለፃ ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር ያላት የዲኘሎማሲ ግንኙነት ታሪክ በአጼዎች ዘመን ጀምሮ የሚመዘዝ መልካም ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሁም ተምሳሌት ሀገር እንድትኾን አስችሏታል። ግንባር ቀደም የዲኘሎማሲ ባለቤትም ነበረች ብለዋል።

በአጼ ምኒልክ የአገዛዝ ዘመን መልካም ግንኙነት በማድረግ የተለያዩ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገራቱ እንዲገቡ ተደረገዋል፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም የፓን አፍሪካን መሪ፣ የአፍሪካ የኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ እንድትሆን ተደረጋለች። ይህ ሁሉ የዲኘሎማሲ ውጤት የተገኘው በጋራ ከልብ በተደረገ ጠንካራ ወዳጅነት እንደኾነ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ወዳጅነት ከሌግ አፍ ኔሽን አባልነት እስከ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት አድርሷታል። በሰንሰለት ተያይዞ እና በሀገር ወዳድ መሪዎቿ ደም ሰርጾ የመጣው ዲፕሎማሲ ዘመን ዘመንን እየወለደ፣ ትውልድ ትውልዱን እየደገመ ቢመጣም ለኢትዮጵያ የዕለት ከዕለት ተግባሯ ኾኖ ቀጥሏል፤ ወዳጅነቷም ከብዙ የወጭ ሀገራት ጋር ተጋምዷል።

ታዲያ የዳበረ የዲኘሎማሲ ባሕል ባለቤት እና ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር የባሕር በር ባለቤትነቷ የሉዓላዊነት እና የሕልውና ጉዳይ እንደኾነ ያስረዳሉ።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው የውጭ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን በተለይም የባሕር በር ጉዳይ ሕልውና ለማስጠበቅ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። ከሀገራት ጋር ያሉት መልካም ግንኙነትም የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ሀገራት ተጽዕኖ እና ጫና እንዲያሳድሩ በር ይከፍታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ቅቡልነት ከፍ ያደርጋል፤ ለዓለም ማኅበረሰብ የሕልውና ጉዳይ መኾኑን የምታስረዳበት ሂደትም ነው። አቋማን ለማሳወቅ እና እንዲደግፋ ዕድል ይሠጣል ነው ያሉት። በተቀናጀ መልኩ ሰላማዊ በመኾነ መንገድ ማስቀጠል እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት።

ለተፈፃሚነቱ መልካም ዕይታን ከጥንት የዲኘሎማሲ ታረክ ጀምሮ የመጣውን እንዲረዱ እና ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት። ይህም የሀገራት በመልካም ዐይኖች እንዲመለከቱት፣ ቅን ልቦች እውነትን እንዲፈርዱ ያደርጋል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ በታረኳ እና በዲፕሎማሲያዊ ማንነቷ የአፍሪካ ቀዳሚ ተምሳሌት እና በዓለም ዓደባባይ የነገሰች መኾኗ ታሪክ የማይረሳው፣ ትውልድ የሚወርሰው ሃቅ ነው ይላሉ።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በፈረንጆች 2026 ከገባ ወዲህ ከበርካታ የውጭ ሀገራት ጋር የውጭ ግንኙነት አድርጋለች። ይህን የዲፕሎማሲ ግንኙነት አጠናክራ በማስቀጠል ብሔራዊ ጥቅሞቿን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

በተለይም ኀያላን ከሚባሉ የዓለም ሀገራት ጋር ጠንካራ የውጭ ግንኙነቶችን በማድረግ በሰላማዊ፣ በውይይት እና በንግግር የባሕር በር ተጠቃሚ ትሩፋቶች እንዱሁም ስኬቶች ባለቤት መኾን ይገባል።

የሀገር ውስጥ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ግንኙነት ማስቀጠል ይገባል ያሉት ዶክተር እምቢያለ የባሕር በር ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋትን በማምጣት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። ኢኮኖሚዋን ፈጣን እና ዘርፈ ብዙ ዕድገቶች እንዲመዘገቡ ያግዛል።

ሁሉም በየዘርፉ የዲፕሎማሲ ተግባርን ለማሳደግ የሀገሪቱ አምባሳደሮች በመኾን ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምርጫው ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleየቶንሲል በሽታ እና መከላከያዎቹ