
ጎንደር: የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
ውይይቱ የምርጫ ዝግጅትን ጨምሮ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ሃሳቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የቅማንት ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ተገኑ ደረጀ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና ነጻ እንዲኾን በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ጊዜ እና በድኅረ ምርጫ ሂደቶች ውጤታማ ሥራዎችን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ገዥው ፓርቲ የላቀ ኀላፊነት እንዳለበት ያመላከቱት የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው ለምርጫ ሂደቱ ምቹ ምኅዳር መፍጠር ይጠበቃልም ነው ያሉት።
ሰላም ለመንግሥት ብቻ የሚተው ጉዳይ ባለመኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሀገር ሰላም ባለቤት መኾን አለበትም ብለዋል።
የሌሎችን ሃሳብ ባከበረ መልኩ ሃሳብን በነጻነት ማንጸባረቅ እንደሚገባም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲን ወክለው በውይይቱ የተገኙት ዝናወርቅ ታደለ በምርጫ ሂደት ሃሳብን በነጻነት በማራመድ የሌሎችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
“የምርጫ ሥርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለውጤታማነቱ በጋራ መሥራት ያስፈልጋልም” ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲን ወክለው በመድረኩ የተገኙት ካሳ በለጠ ካለፉት የምርጫ ሂደቶች ተሞክሮዎችን መውሰድ ይጠበቃል ብለዋል።
ምርጫው ውጤታማ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን በጋራ መሥራት ስላለው አስፈላጊነት አንስተው በጋራ እንሥራ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ፓርቲው ልዩ ልዩ የቅድመ ምርጫ ሂደቶችን እየተገበረ መኾኑንም አንስተዋል።
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በዕኩል ተደራሽነት ዕቅዳቸውን እንዲያስተዋውቁ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
