ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሂደት የሚገነባ ነው።

13

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ምርጫ ዜጎች በየደረጃው የሚገኙ የሕዝብ ተወካዮችን እና መሪዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በድምጽ አሰጣጥ የሚመርጡበት ሥርዓት ነው። የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄድ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡

ለመኾኑ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምንድን ነው?

‎በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሐሳቡ ተስፋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለት ሕዝባዊ አሥተዳደር ሲኾን ሕዝብ በመረጠው የመንግሥት ሥርዓት ሲተዳደር ነው ይላሉ፡፡ ዴሞክራሲ ሕዝቦች ለራሳቸው፣ በራሳቸው፣ ከራሳቸው የሚመርጡበት ሥርዓት መኾኑን ተናግረዋል፡፡

‎ሕዝብ የራሱን አሥተዳዳሪዎች ሲመርጥ ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን መርሆወች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ እና ተአማኒ መኾን አለበት ብለዋል፡፡

‎ነጻ ምርጫ ሲባል ያለተጽዕኖ መራጮች የፈለጉትን የሀሳብ አማራጭ፣ ይጠቅማል የሚሉትን ሰው በነጻነት መምረጥ ማለት ነው፡፡

‎ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ብቻ ባለመኾኑ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና ድኅረ ምርጫ ሁነቶች ላይ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ሀሳባቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት ሜዳ በነጻ ያለጫና ክፍት መኾን እና ለተፎካካሪዎች ሜዳው እኩል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህም ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡

ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ ከኾነ ተአማኒነት ይኖረዋል፤ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ደግሞ ውጤቱን ሕዝቡ እንዲቀበለው እና ተግባራዊ እንዲያደርገው ያግዛል ነው ያሉት።

‎በምርጫ ውስጥ ዋና ዋና የሚባሉት ተዋናዮች መራጭ ሕዝብ፣ ተመራጭ እጩዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውስጥ ምርጫውን የሚያሳልጡ አካላት እንዳሉ አብራርተዋል። ለአብነትም መንግሥት፣ መገናኛ ብዙኀን እና የሲቪክ ማኅበራት እንደሚጠቀሱም አንስተዋል፡፡

‎ተመራጮች በግላቸው ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወክለው የሚቀርቡ ሲኾኑ በአብዛኛው የፖሊሲ ባለቤቶች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ተዋናይ ናቸው ብለዋል፡፡

‎ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከማን ምን ይጠበቃል?

‎👉 ከፖለቲካ ፓርቲዎች፡-

ሕዝብ የሚመርጠውን የሚወስነው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የፖሊሲ አማራጮች በመኾኑ ፖሊሲያቸውን በነጻነት እና ያለ ገደብ እንዲያቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ፓርቲዎችም ፖሊሲያቸውን በግልጽ፣ ሕጋዊ በኾነ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሕዝቡ ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

‎👉 ከመንግሥት፡-

የሕግ አካላት፣ ምርጫ ቦርድ እና ፍርድ ቤትን የመሰሉ ሚዛን ማስጠበቂያ ተቋማት ለምርጫው ፍትሐዊነት እና ምቹ ኹኔታ እንዲፈጠር ተግተው እንዲሠሩ መንግሥት መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

‎👉 ከሕዝብ፡-

የፖሊሲ አማራጮችን በማየት፣ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለውጥ ይመጣል የሚል አስተሳሰብ በመያዝ ሕዝብ በምርጫው መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‎ለዚህም ተወዳዳሪዎች የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች በንቃት በመከታተል፣ በመራጭነት መመዝብ፣ የምርጫ ካርድ አውጥቶ ይበጀኛል የሚለውን መምረጥ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰቡ መልካም እሴቶች እንዲያድጉ በመሥራት ሀቀኛ ዜጎች የምርጫ አሥፈጻሚ እንዲኾኑ መታገል እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

‎ዴሞክራሲ በአንዴ የሚገነባ አይደለም ያሉት ምሁሩ ዴሞክራሲያዊ ባሕል በየጊዜው እየተተገበረ በሂደት የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሊኖረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

‎ዴሞክራሲ የእሴት ግንባታ በመኾኑ ጊዜ ይወስዳል፤ ተገንብቶ የሚጨረስ ሳይኾን አዳዲስ ፍላጎቶች ሲመጡ ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ እየተገነባ የሚቀጥል መኾኑን ገልጸዋል፡፡

‎የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወጥነት የለውም፤ በተለያዩ ሀገራት ከማኅበረሰቡ ሥነ-ልቦና እና ነባራዊ ኹኔታ ጋር በተቃኘ መልኩ የሚገነባ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ ሊኾኑ ይገባል።
Next articleተማሪዎችን ለሀገር እና ለክልል አቀፍ ፈተናዎች ብቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው።