ወጣቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ ሊኾኑ ይገባል።

4

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ሕዝቦች ሰላም እና ደኅንነትን ያስጠብቅልኛል፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያሰፍንልኛል፤ የኢኮኖሚ እና የልማት ተጠቃሚ ያደርገኛል፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ያስከብርልኛል ያሉትን መሪ ለመምረጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ነው።

በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲከናወን ግብዓቶችን የማቅረብ፤ ስለምርጫው ግንዛቤ የመፍጠር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ወጣት ጌታሰው መለሰ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ነው። ምርጫ ለአንዲት ሀገር እና ለሕዝቦቿ ወሳኝ ነገር መኾኑን አንስቷል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቀድሞ ካርድ ለማውጣት፤ ይመራኛል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥርልኛል፤ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ያደርገኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ለአሚኮ ተናግሯል።

ምርጫ የፓለቲካ ጉዳይ ሳይኾን የነጻነት እና የዴሞክራሲ መገለጫ መኾኑን አንስቶ ወጣቶች ምርጫ ካርድን በማውጣት እና በመምረጥ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ፓርቲ እንዲመርጡ አመላክቷል።

ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን የሁሉም ፍላጎት ነው ያለችው ደግሞ ወጣት የዓለምወርቅ ደበላ ናት። ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከወጣቶች ተሳትፎ ባሻገር ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ጥያቄ በማይፈጥር እና ግጭትን በማይቀሰቅስ መንገድ መኾን አለበት ነው ያለችው።

ወጣቶች የተሻለ ሕይዎት የሚሰጣቸውን፤ የሀገር ዕድገት ያመጣል ብለው የሚያምኑትን አካል በትኩረት ሊመርጡ እንደሚገባም አንስታለች።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የወጣቶች ዘርፍ ኀላፊ ዘላለም አረጋ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ የሚኖረው ወጣቶች በምርጫው ሂደት ተሳታፊ ሲኾኑ ነው ብለዋል።

ወጣቶች በታዛቢ እና በመራጭነት መሳተፍ እንዳለባቸውም አንስተዋል። ወጣትነት አፍላ እድሜ መኾኑን አንስተው ሰከን ብሎ ነገሮችን ማየት እና መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከሀሰተኛ መረጃ በመቆጠብ እና ሚዛናዊ በመኾን በምርጫ ሂደቱ ተሳታፊ እንዲኾኑም አሳስበዋል።

የወጣቶች ማኅበራት በአደረጃጀታቸው መሠረት በምርጫ ሂደቱ ለመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወኑ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጦርነት የወደመው የአዳርቃይ ሆስፒታል ሙሉ ጥገና ሊደረግለት ነው።
Next articleዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሂደት የሚገነባ ነው።