
ባሕርዳር፡ የካቲት 17/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ “በሴቶች ተሳትፎ የፀናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የሴቶች መድረክ በባሕርዳር አካሂዷል።
የኢፌዴሪ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ እና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ሥራ አሥፈጻሚ ሂክማ ከይሬዲን ብልጽግና ፓርቲ ትናንትን ማረም፣ ዛሬን መሥራት እና ለመጭው ትውልድ ምቹ የኾነች ኢትዮጵያን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ በሕዝብ ዘንድ ታማኝነት እና እኩልነት ያለው እንዲኾን ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመምረጥ፣ በመመረጥ እና በመታዘብ ደረጃ ያላቸውን ሚና አጉልተው እንዲያወጡም አሳስበዋል።
በአብሮነት እና በተደመረ እሳቤ ውስጥ ኾኖ ሀገር ለማቅናት ምርጫ ትልቅ መሳሪያ መኾኑንም ገልጸዋል። “የሰላም ባለቤቱ ግለሰቡ ራሱ ነው” ያሉት ሚኒስቴር ድኤታዋ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ ደግሞ ኢትዮጵያ ባላት የብልጽግና ጉዞ ሴቶች በልማት፣ በሰላም እና በዴሞክራሲ ግንባታ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ ራሳቸውን እና ማኅበረሰቡን እንዲጠቅሙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር እና እንደ ክልል ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና የሁሉንም ማኅበረሰብ ይኹንታ ያገኘ እንዲኾን ሴቶች ብቻ ሳይኾኑ ሁሉም ማኅበረሰብ ለሰላም እንዲሠራ ነው ያሳሰቡት።
ከፋፋይ ትርክቶችን ወደ ጎን የሚያስቀሩ እና ሰላምን የሚያመጡ ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሴ ሴቶችን መደገፍ፣ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን የነቃ እና የበቃ ማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለሴቶች የነቃ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት መስጠት ደግሞ የሁሉም ድርሻ ሊኾን እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የመድረኩ ተሳታፊ በሰሜን ጎጃም ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ነጻነት ሲሳይ ደግሞ ምርጫ ለማካሄድ ሰላም አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።
ለቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫም ሰላምን ማስቀደም እና የሰላም አምባሳደር መኾን እንደሚገባ ነው የገለጹት። ሰላምን ለማጽናትም የሴቶች ሚና እና ተሳትፎ ወሳኝ እንደኾነም ነው የጠቀሱት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
