
ባሕር ዳር: የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል አገልግሎት ማሻሻያ ዕቅድ ነው፡፡ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2030 ታላቅ ልማትን በማስመዝገብ በምጣኔ ሃብት፣ በመንግሥታዊ አሥተዳደር እና በማኅበራዊ ዘርፎች ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነው።
ዓለም በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና እድገት ታግዞ በሚያደርገው የውድድር ጉዞ የሰዎች ሕይወት ቀላል እና ምቹ እየኾነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም በሥልጣኔው ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለመኾን ዓለም የደረሰበትን እና የሚጓዝበትን መንገድ መጓዝ እና መወዳደር የሉዑላዊነት ግዴታ ነው፡፡
የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን፤ ንግድን እና የፋይናንስ ግብይትን ዲጂታል ማድረግ፤ ዲጂታል ክህሎትን ማሳደግ እና የሳይበር ደኅንነትን አስተማማኝ ማድረግ ከሚጠቀሱ ግቦቹ ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 ልታሳካው ያቀደችው ስትራቴጂ ነው፡፡ ከግብርና፣ ከኢንዱሥትሪ፣ ከማዕድን እና ከቱሪዝም ልማት ዘርፉም ተስተካክሎ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡
ግቦቹም ተደራሽነትን ማስፋት፣ እኩል ዕድል መፍጠር እና በዜጎች እና ተቋማት መካከል መተማመንን መፍጠር መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ሥራ አሥኪያጅ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያ ሥላሴ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዓላማ ዲጂታላይዜሽንን በገጠሩ በማስፋት እና በማሳደግ ሁሉም የዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም ከተሞች የመሶብ አገልግሎት መስጫ ማዕከል መፍጠር፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ዲጂታል አይዲ፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ማሳደግ፣ ኢ- ገቨርናንስ፣ ኢ-ኮሜርስን ማስፋት እና ማጠናከር የ2030 ተጠቃሽ ግቦች መኾናቸውንም ጨምረዋል፡፡
አቶ ዮዳሄ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተጀመሩ ዲጂታል መታወቂያ፣ ኢትዮ ኮደርስ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይትና ክፍያዎች፣ አድራሻዎችን በዲጂታል ሥርዓት ለይቶ መያዝ፣ የመሬት ካርታ እና አሥተዳደር ሥርዓት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እርሾ መጣላቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሞባይል ዳታ ዋጋ መቀነስ፣ የሞባይል ካርድ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር መጨመር፣ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች መፈጠር እና ማደግም የዲጂታል 2025 ውጤቶች እና እርሾዎች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኔትወርክ አቅርቦት እና ተደራሽነትን ማሳደግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ምሰሶዎች መኾናቸውንም አክለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
