
አዲስ አበባ፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሀገር የተንሰራፋውን ሕገ ወጥ ንግድ ለመግታት ቅንጂታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ “ሕገ ወጥ ንግድን እናስቁም፤ የሥራ ዕድል፣ ገቢን እና ሀገራዊ ደኅንነትን እንጠብቅ” በሚል መሪ መልዕክት አራተኛውን የፀረ ሕገ ወጥ ንግድ ጉባኤ አጋር እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ዐይናለም ዓባይነህ (ዶ.ር) ሕገ ወጥ ንግድ የሀገር ውስጥ ገቢን በማቀጨጭ ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት ኾኗል ብለዋል፡፡
መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን በመጨር የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ቢሠራም ሕገ ወጥ ንግድ በሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መኾኑንም አክለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባለፉት ሦሥት ዓመታት ባካሄዳቸው ሦሥት ጉባኤዎች ሕገወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ላይ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
አራተኛው ጉባኤ ወደ መፍትሄ ትግበራው በመግባት በቅንጅት የሚሠራበት መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ቀነኒስ ለሜ (ዶ.ር) በበኩላቸው የጉባኤው ዋና ዓላማ ሕገ ወጥ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ የሚደርሱ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ሕገ ወጥ ንግድን ለመግታት የሁሉንም እርብርብ የሚጠይቅ በመኾኑ ሕጋዊ መስመርን ተከትለው እንዲሠሩ በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲኾን በኢትየጰያ ሕገ ወጥ ንግድ ከተንሰራፋባቸው ዘርፎች መካከል የእንሳት ንግድ፣ የመድኃኒት እና የቡና ምርት ንግድ ዋና ዋናዎቹ መኾናቸውም ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
