የአኗኗር ዘይቤ ለስኳር በሽታ መጋለጥ ከፍ ያለ ድርሻ አለው።

12

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
ወይዘሮ አያልነሽ ሙላት ይባላሉ፡፡ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ለረጅም ዓመታት የስኳር በሽታ ሕመምተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሠርተው ልጆቻቸውን በሚንከባከቡበት ዕድሜ ላይ በዚሁ በሽታ ምክንያት ለዐይነ ስውርነት እንደተዳረጉ ነው የተናገሩት፡፡

ወይዘሮ አያልነሽ እንዳሉት በአብዛኛው መቀመጥ የበዛበት ሥራ መሥራታቸው፣ የአመጋገብ ሥርዓታቸው እና ከሰውነታቸው ከፍተኛ ውፍረት ጋር ተዳምሮ በበሽታው እንዲጠቁ ምክንያት እንደኾነ እና በቶሎ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አገልግሎት አለማግኘታቸው ደግሞ ለዐይነ ስውርነት እንደዳረጋቸው ሐኪሞች እንደነገሯቸው ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮዋ ዐይኔን ካጣሁ እና በልጆቸ ድጋፍ ስር መኖር ከጀመርኩ ከ23 ዓመታት በላይ ኾኖኛልም ብለዋል፡፡

የስኳር በሽታ ከዘር ብቻ አይመጣም የኑሮ ዘይቤ ትልቅ ሚና አለው ያሉት በፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሐኪም ዶክተር እስከዳር ስለሽ ናቸው፡፡

እንደ ዶክተር እስከዳር ገለጻ የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን ከመደበኛው ቁጥር በላይ ሲጨምር የሚከሰት ሕመም ሲኾን ይህም ሰውነት ኢንሱሊንን በበቂ መጠን ማመንጨት ካልቻለ ወይም የተፈጠረውን ኢንሱሊን በትክክል መጠቀም ካልቻለ ነው ብለዋል።

ኢንሱሊን የደም ስኳርን ወደ ህዋሳት በማስገባት ለኀይል እንዲውል የሚረዳ አስፈላጊ ሆርሞን መኾኑንም አብራርተዋል።

ሕመሙ በዋናነት በሁለት ይከፈላል ያሉት ዶክተር እስከዳር አንደኛው ኢንሱሊን የሚያመርቱ ሴሎች ሲጎዱ እና ማመንጨት ሲቋረጥ የሚከሰት ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ሰውነት ኢንሱሊንን በትክክል ሳይጠቀም ወይም በቂ መጠን ሳይፈጥር የሚመጣ ነው ብለዋል፡፡ ከተጠቀሱት ውስጥ ሁለተኛው የስኳር አይነት በአብዛኛው ሰዎች ላይ ይከሰታልም ነው ያሉት፡፡

“የስኳር በሽታ በዘር ሊተላለፍ ይችላል” የሚሉት ዶክተር እስከዳር በቤተሰብ ውስጥ እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት አለፍ ካለ እስከ አያት ሊሄድ የሚችል ታማሚ ካለ የመያዝ ዕድሉ ይጨምራል ነው ያሉት።

ከእነዚህ በተጨማሪም፡-

👉የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ

👉የተለያዩ ኢንፌክሽኖች ጣፊያ ውስጥ ያሉ ኢንሱሊን አምራች ሴሎችን ሲያጠቁ እና

👉ጤናማ ያልኾነ የአመጋገብ ሥርዓት መኖር የስኳር በሽታን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ሐኪሟ ማብራሪያ የስኳር ታማሚ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፦

👉ብዙ መሽናት

👉ከፍተኛ የውኃ ጥም

👉ድካም

👉ያልተጠበቀ ክብደት መቀነስ እና

👉ቁስል በተሎ አለመዳን የሕመሙ ዋና ምልክቶች ናቸው።

ይህንን በሽታ በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ የልብ ችግር፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የዐይን ብልሽት እስከ ዐይነ ስውርነት ድረስ እና የነርቭ ጉዳት እንደሚያስከትልም ነው ያብራሩት።

የስኳር በሽታ መከላከያ መንገዶቹ፦

👉ጤናማ አመጋገብ መከተል በተለይ ጨው፣ ጮማ እና ስኳር የበዛበት ምግብ አለመመገብ።

👉አመጋገባችን አትክልት እና ፍራፍሬ የበዛበት እንዲኾን ማድረግ።

👉መደበኛ እንቅስቃሴ ማድረግ በትንሹ በሳምንት 150 ደቂቃ የሚኾን ወይም በቀን ለ30 ደቂቃ ለ5 ቀናት ያክል ማድረግ።

👉የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር እና

👉የደም ስኳር መጠን ቅድመ ምርመራ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መኾኑን አስገንዝበዋል።

ሕመሙ ሙሉ በሙሉ መዳን ባይችልም ምልክቶች በሚኖሩበት ጊዜ በፍጥነት በአቅራቢያ በሚገኝ የሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ እና በትክክለኛ ክትትል በመቆጣጠር ጤናማ ሕይወት መኖር እንደሚቻልም ዶክተር እስከዳር ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደሮ እርባታ ተሰማርተው እየሠሩ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው።
Next articleየመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም መስፈን፤ ለጋራ ልማት እና ተጠቃሚነት ሊሠሩ ይገባል።