
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ የማይቀለብስው፤ የዓለምን ትኩረት የሰረቀው፤ የአይቻልምን መንፈስ እንዳይነሳ አድርጎ የቀበረው፤ ለአዕላፍት የተስፋ ብርሃንን የሰነቀ ታሪክ በሰው ዘር መገኛ ሀገር ተከሰተ።
ዐይኖች ሁሉ ወደ አፍሪካ ወደ ፀሐይ መውጫ ተመለከቱ፤ ጆሮዎች ሁሉ የተፈጸመውን ገድል ለመስማት በተጠንቀቅ ቆሙ፤ አንድነት፤ አልሸነፍ ባይነት፤ የነጻነት ትግል፤ የሕይወት መስዋዕትነት በታላቋ የኢትዮጵያ ምድር በዓድዋ ሰማይ ሥር በደማቁ ታዬ።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 በተሰኘ መጽሐፋቸው የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ አንድ ትልቅ ድርጊት እንደመኾኑ ኹሉ የቅኝ ገዥዎችን ቅስም የሰበረውን ያህል የተገዥዎችን አንገት ከተደፋበት ቀና እንዲል ያደረገ ክስተት ነበር ብለውታል።
ዓድዋ አፍሪካ በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሰራፋችው በአውሮፓ ላይ ያደረገችው ፈር ቀዳጅ የነጻነት ምዕራፍ መኾኑንም ይገልጻሉ። ዓድዋን ልዩ ትኩረት ያሰጠው ጥቁሮች በነጮች ላይ የተጎናፀፉት የመጀመሪያው ዐቢይ ወታደራዊ ድል በመኾኑ ነው።
የዓድዋ አብነት በተለይም የነጮች የበላይነት ከአስከፊ የዘር መድልዎ ፖሊሲ ጋር በተቆራኘባቸው አካባቢዎች በደቡባዊ አፍሪካ እና በአሜሪካ ሀገሮች ለሚገኙ ጥቁሮች የዓድዋ ባለድል የኾነችው ኢትዮጵያ የነፃነት እና የክብር ፋና ኾነች። ባደረገችው ተጋድሎም ለዓለም የጥቁር ሕዝቦች መብት መከበር መሠረት ኾናለች።
ኢትዮጵያን ምሳሌ በማድረግም አቢሲኒያ፤ ኢትዮጵያ እና ኮፕቲክ በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩ አያሌ አብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ንቅናቄዎች በተለይ በአሜሪካ አህጉር መቋቋማቸውን በመጽሐፋቸው ከትበዋል።
ከኢትዮጵያ በወሰዱት ትምህርትም ጆሞ ኬንያታ እና ክዋሜ ንክሩማህ የመሳሰሉትን ወጣት አፍሪካዊ መሪዎች ጥቆሮችን ለማስተባበር የ«ፓን አፍሪካኒዝም›› እንቅስቃሴ በማቋቋም ከአሜሪካ አህጉር ወደ አፍሪካ አሸጋግረዋል፡፡
ቆይቶም በ1955 ይህ በከፊል በዓድዋ ድል የተቀሰቀሰው አብዮት ድሉ በተገኘበት ሀገር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ታሪካዊ ድምዳሜው ላይ መድረስ ተችሏል።
ኢትዮጵያም የቀድሞውን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረት በማቋቋም ረገድ ጉልህ ሚናን ተወጥታለች። የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነትም ድርጂቱ ሲመሠረት ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴን በመሪነት እንዲመረጡ አድርጓል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ግዛቸው ዐቢይአለ ኢትዮጵያ የሰው ልጆች ዘር መገኛ፤ የአፍሪካ የታሪክ ዕውነት መነሻ፤ የነጻነት ጎህ፤ የአፍሪካዊነት አስኳል መኾኗን አንስተዋል።
ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳየች ሀገር መኾኗንም ተናግረዋል። ለዓለም ሕዝቦች የእኩልነት እና የሰብዓዊነት መነሻ መኾኗንም ጠቁመዋል። ጥቁር ሕዝቦች ጭቆናን እንዲጠሉ፤ ለመብታቸው እንዲታገሉ፤ ቅኝ ግዛትን እንዲጸየፉ፤ እኩልነታቸውን እንዲያረጋግጡ፤ በምድራቸው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ፤ በጸጋቸው እንዲጠቀሙ ኢትዮጵያ በዓድዋ ምድር ነጮችን በማሸነፍ ለአፍሪካውያን የማንቂያ ደወል ኾናለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ አሸናፊነትን ማሳየት ብቻ ሳይኾን አፍሪካዊ አንድነት እንዲፈጠር አድርጋለች ያሉት መምህር ግዛቸው የአፍሪካ ኅብረትን በማቋቋም ለአፍሪካ እና ለጥቁሮች መብት መከበር ጉልህ ድርሻ መወጣቷን እንደ ማሳያ አንስተዋል።
ጥቁር ሕዝቦች በአንድነት እንዲሠበሠቡ፤ ለኢ-ፍትሐዊነትን እንዲታገሉ፤ በዝባዥነትን እና ኃላ ቀርነትን እንዲታገሉ ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ መኾኗን ጠቁመዋል። እንደ ማርከስ ጋርቤ፤ ኔልሰን ማንዴላ የመሳሰሉ የጥቁር ሕዝብ መብት ተሟጋቾች ኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ አድርገው ለጥቁር ሕዝቦች መታገላቸውን አንስተዋል።
ከዓድዋ ድል በኃላ በርካታ አፍሪካውያን የሀገራቸውን አርማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች መውሰዳቸውን፤ መንገዶቻቸውን፤ ምርታቸውን በኢትዮጵያ መሪዎች ስም መሰየማቸው ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች ምሳሌ መኾኗን ማሳየ እንደኾነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የኃላ ታሪኮችን በአግባቡ መረዳት ከተቻለ ለወደፊቱ መጻዒ ዕድል መሠረት ነው ያሉት መምህር ግዛቸው ትውልዱ የአባቶቹን ታሪክ በአግባቡ ማጥናት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ታሪክን በአግባቡ በማጥናት እና በመመርመር ሀቅ ላይ የተመሠረተ የሀገር ግንባታ ማከናወን፤ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር፤ ብሔራዊ ትርክትን መገንባት እና ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
