“130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቅቋል” የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ.ር)

12

 

አዲስ አበባ፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በድምቀት ለማክበር የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ.ር) “130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በላቀ ድምቀት ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቅቋል” ብለዋል።

የድል በዓሉ “ዓድዋ 130 ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ መልዕክት ነው የሚከበረው።

ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ የዓድዋ ድል የአንድ ወቅት የጦርነት ድል ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያውያን የማይበገር ማንነት ማኅተም፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና እና የሰው ልጆች እኩልነት የተረጋገጠበት ዓለም አቀፋዊ ድል መኾኑን አብራርተዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ የዘንድሮው በዓል የኢትዮጵያዊነትን የጥንካሬ እና የጽናት መሠረት ዳግም የምናድስበት እንዲሁም ለሀገራችን ሉዓላዊነት እና አንድነት የገባነውን ቃል ኪዳን የምናፀናበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

“ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” የሚለው መሪ መልዕክትም ትናንት በጀግኖች መስዋዕትነት የተጠበቀችውን ሀገር ዛሬ በዘላቂ ሰላም እና ልማት ወደ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ከፍታ ለማሻገር ያለንን ቁርጠኝነት የሚገልጽ ነው።

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የዓድዋን የጀግንነት ውርስ በመሰነቅ፣ የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ወደ ተስፋ ሰጭው ብሩህ አድማስ የሚደረገውን ጉዞ ለመጠበቅ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ መኾኑን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ አረጋግጠዋል።

የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ሕዝቦች የጋራ ድል በመኾኑ፣ በዓሉ የፓን አፍሪካኒዝምን መንፈስ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል ነው ያሉት። ይህንን ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ በዚሁ የበዓል ሳምንት ሁለተኛውን የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ሥብሠባ የምታስተናግድ መኾኑ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገው ነው ያስረዱት።

ይህ መድረክ ዓድዋ የቅኝ ግዛት ቀንበርን የሰበረ የነፃነት አርማ መኾኑን በዓለም አደባባይ ዳግም የሚያረጋግጥ ይኾናልም ነው ያሉት።

በዓሉን አስመልክቶ በርካታ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ክንውኖች የተዘጋጁ ሲኾን ከእነዚህም መካከል፦

👉”የዓድዋ ድምፆች” በሚል የሚካሄዱ የወጣቶች መድረኮች

👉ስፖርታዊ ውድድሮችና እና የወታደራዊ እና ታሪካዊ አውደርዕይዮች

👉ልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች እና የዓድዋን ድል የሚዘክሩ ዘጋቢ ፊልሞች ይገኙበታል።

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች በሙሉ እንኳን ለ130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለትም ሚኒስትሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከስሜት የጸዳ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው።
Next articleምርጫ በማስተጓጎል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩትን መታገል ይገባል።