
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች የሥልጣን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት፣ የሰብዓዊ ክብራቸው እና የሥነ-ልቦና ነፃነታቸው ምንጭ መኾኑ ይታመናል። ይህ ሂደት ፍትሐዊ፣ እና ከስሜት የጸዳ ይኾን ዘንድ ደግሞ የምሁራን ሚና ላቅ ያለ ድርሻ እንዳለው ይጠቀሳል።
ምርጫ ለአንድ ዜጋ ድምጽ የመስጠት መብት ብቻ ሳይኾን የሀገርን ዕጣ ፈንታ የመወሰን እና ለቀጣዩ ትውልድ የዳበረ የዴሞክራሲ ባሕልን የማስረከብ መሠረት ነው።
ግለሰቦች በሰጡት ድምጽ ሀገራቸውን የሚመሩበት፣ ማኅበረሰቡ በሰላም አብሮ የሚኖርበት እና ተተኪው ትውልድ የተከበረች ሀገርን የሚረከብበት ዋስትና እንደኾነም ይነገራል።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ አየነው ፈንታ (ዶ.ር) እንደሚሉት ምሁራን በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉልህ ድርሻ አላቸው።
በተለይም በምርጫ ወቅት ዜጎች በዕውቀት እና በዕውነት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ ኖሯቸው በንቃት እንዲሳተፉ የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው።
ዶክተር አየነው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት፣ ምሁራን በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፦
ምሁራን ለየትኛውም ወገን ሳይወግኑ፣ ጥልቅ ዕውቀታቸውን በመጠቀም ለሕዝብ እና ለሀገር የሚበጀውን ምልከታ በግልጽ መተንተን እና ማስረጽ ይኖርባቸዋል።
መራጮች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው፣ በስሜት ሳይኾን በመረጃ ላይ ተመስርተው የሚወክላቸውን ፓርቲ እንዲመርጡ ታማኝ መረጃዎችን ማድረስ የሙያ ግዴታቸው ነው።
ምሁራን በመራጭነትም ኾነ በተመራጭነት በመሳተፍ፣ ሀገራዊ ሕግ እና ሥርዓትን ተከትለው ለሌላው ማኅበረሰብ ግንባር ቀደም አርዓያ መኾን ይጠበቅባቸዋል።
ዜጎች የተለያዩ ፓርቲዎችን ሀገራዊ ፋይዳ፣ የልማት ተልዕኮ እና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት አቋም መዝነው እንዲመርጡም ምሁራዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባል።
በአጠቃላይ የዜጎች መብት እና ጥቅም የሚከበርባት፣ መተሳሰብ እና አብሮነት የነገሰባት እንዲኹም ልማት የተረጋገጠባት ሀገር መገንባት የሚቻለው ነፃ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ሲከናወን መኾኑን ዶክተር አየነው ገልጸዋል።
ለዚህም ስኬት ምሁራን ከቡድንተኝነት በጸዳ መልኩ፣ ለሙያቸው እና ለሀገራቸው ያላቸውን ታማኝነት በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
