
ባሕር ዳር: 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ነው።
በምርጫ ወቅት ዜጎች ስለ መራጭነት መብታቸው እና ስለ ምርጫው ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ትምህርት በመስጠት ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። በምርጫ ሂደት ውስጥ ገለልተኛ ታዛቢዎችን በማሠማራት ሂደቱንም ይከታተላሉ።
ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ድምጽ ቆጠራ ድረስ በሕግ እና በሥርዓት መከናወኑን በማረጋገጥ ለሂደቱ ተዓማኒነት ማረጋገጫን ይሰጣሉ።
ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ቅሬታዎች በሕጋዊ መንገድ እንዲፈቱ ግፊት ያደርጋሉ። በሕዝብ፣ በመንግሥት እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ግልጽነት እንዲኖር እንደ ድልድይ በመኾን ያገለግላሉ።
በቀጣይ ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ ሕይወት ሪሀብሊቴሽን ሪኢንተግሬሽን አሶሴሽን ዳይሬክተር አብዱረሐማን ከማል ድርጅታቸው በትምህርት እና ቅስቀሳ ዘርፍ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ያገኘ መኾኑን ተናግረዋል። ባለፉት ምርጫዎች በመሳተፍ ያገኙትን ልምድ በመጠቀም ኅብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ይኾነኛል የሚለውን በነጻነት እንዲመርጥ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዝግጅት ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።
በየአካባቢው ተደራሽ በመኾን በቂ የትምህርት እና ቅስቀሳ ለማድረግ የሚያስችሉ በየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልኾኑ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎች በመመልመል ስምሪት እየሰጠን ነው ብለዋል። የምርጫ ሂደቱን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ኅብረተሰቡ ወጥቶ የመምረጥ ባሕሉን እንዲያዳብር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የሥርዓተ ጾታ ማኅበር ሰብሳቢ ማሕሌት ሽፈራው ማኅበሩ በመራጮች ትምህርት መሥጠት ዙሪያ በምርጫ ቦርድ እውቅና ማግኘታቸውን አብራርተዋል። ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሟላ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው አሠራር መሠረት የሰነድ ዝግጅቶችን አጠናቅቀናል ብለዋል።
ስለ ምርጫው ማስገንዘብ፤ በተለይም ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች በምርጫ ሂደቱ በንቃት እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩም አንስተዋል። ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ትብብርን በመፍጠር አዳዲስ አማራጮችን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በዝግጅት ላይ ስለመኾናቸው ነው የገለጹት። በቀጣይ ሳምንታት ወደ ተግባር እንደሚገቡም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
