
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከለካያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ እና የሰሜን ምእራብ እዝ የሠራዊቱ መሪዎች እና አባላት 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በባሕርዳር አክብረዋል።
በዝግጅቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን እና የመላው የጥቁር አፍሪካ የጋራ ታሪክ መኾኑን ገልጸዋል። ጀግንነታችን እና ስነ ልቦናችን ከቅድመ አያቶቻችን አልገዛም ባይነት የመጣ የኢትዮጵያውያን የማንነታችን መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
ቅድመ አያቶች ባላቸው መሣሪያ እና ሞራል ሀገራችንን እናስከብራለን ብለው በጦርና በጎራዴ ጠላትን ተፋልመው ድል ማምጣታቸውን ገልጸዋል። አሁንም የአያቶቻችን ወኔ ተላብሰን ሀገርን የሚያስከብሩ ግዳጆችን እየተወጣን ባስመዘገባቸው ድሎች እና በነበረን ስነ ምግባር የኩሩ ሕዝቦች ልጆች መኾናችንን አስመስክረናል ነው ያሉት ፡፡
ሰላም የተቃና ሥራ ለመሥራት እና ኢኮኖሚ እንዲያድግ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ፍላጎታችን ከጎረቤቶቻችን ጋር አብሮ ማደግ ነውም ብለዋል ፡፡
በዓሉን በጋራ ስናከብር ለሀገራችን የገባነውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ፣ አያቶቻችን የሰሩትን የታሪክ አንድነት እና የአሸናፊነት መንፈስን በመላበስ፣ የሀገራችን ዕድገት የማይመኙ የውስጥ ባንዳ እና የባዕዳንን እኩይ ተልዕኮ በመመከት ልማቷን በማስቀጠል መኾን አለበት ነው ያሉት።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም የዓድዋ ድል መከበሩ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ መኾኑን ገልጸዋል። ያለፈውን አኩሪ ታሪክ እየረሱ ሀገርም ለባዕዳን አሳልፈው እየሰጡ ላሉ ኀይሎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለታሪካዊ ጠላቶችም ኢትዮጵያን መንካት ምላሹ ምን እንደሚሆን የሚያስገነዝብ መኾኑን አንስተዋል።
ከምሥራቅ እዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው
አዲሱ ትውልድ ክብሯን ጠብቃ የቆየችውን ሀገራችን ሰላሟን ማስቀጠል እንደሚገባው ያመላከተ የድል በዓል ነው ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
