
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ሀገር፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አብሮነት ሊጸልዩ በአንድነት እጆቻቸውን ወደ ፈጣሪ አንስተዋል።
የሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ነብሳቸውን በስጋቸው ላይ ሊያሠለጥኑ የስጋ ፍላጎቶቻቸውን ገትተው የሃይማኖታቸውን ሥርዓት ጠብቀው ለጸሎት ቆመዋል።
በጾም ወራቶቻቸው እርስ በእርስ በመደጋገፍ፤ የተቸገረን በመርዳት፤ የታመመን በመጠየቅ ፤ የተራበን በማብላት፤ በጎ ተግባርን በማከናወን ነብሳቸውን ለፈጣሪ ንጹሕ ያደርጋሉ። በተግባርም ሃይማኖታቸውን ይገልጣሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዐቢይ (ሁዳዴ) ጾም እና በእስልምና ሃይማኖት የረመዳን ጾም በአንድነት ሲጾሙ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ስሜትን ይሰጣሉ። የአብሮነት፤ የመቻቻል፤ የመተሳሰብ ስሜት ጎልቶ ይታይባቸዋልና።
ታላላቆቹ አጽዋማት በአንድ ወቅት እየተጾሙ ነው። የሃይማኖት አባቶችም አማኞች ፍቅር እና ሰላምን፤ አብሮነት እና አንድነትን በተግባር እንዲገልጡ እያስተማሩ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የደብረ ማርቆስ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ ርዕሰ ርዑሳን አባ ኃይለ ማርያም ታገለ ጾም ከመከራ ለመዳን፤ የነብስ እና የስጋን በረከት ለመቀበል፤ ራስን ለመግዛት የሚከወን ሃይማኖታዊ ሥርዓት መኾኑን ገልጸዋል።
ጾም ከፈጣሪ ጋር መገናኛ መሥመር ነው ያሉት ርዕሰ ርዑሳን አባ ኃይለ ማርያም ጾም ክፉ ተግባርን ከመፈጸም፣ መጥፎ ተግባርን ከማከናወን መከልከል ነው ብለዋል።
ጾም የነብስን ቁስል ታድናለች፤ የስጋ ፍላጎትን ትቆርጣለች ነው ያሉት። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከኃጢያት ለማዳን መጾሙንም አንስተዋል።
የዐቢይ ጾም ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንጦስ የጾመው በመኾኑ አማኞች ክርስቶስ ለሰው ልጅ የከፈለውን መስዋዕትነት በማሰብ ይጾማሉ ነው ያሉት።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ሼህ ሙሃመድ ኢብራሂም የረመዳን ወር ከእስልምና ሃይማኖት ማዕዘናት ውስጥ አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
የረመዳን ጾም የተራቡትን የምናበላበት፣ የተቸገሩትን የምንረዳበት እና ከአሏህ ጋር የምንቀራረብበት መንገድ ነው ብለዋል። ረመዳን የበጎነት መገለጫ ወር እንደኾነም አንስተዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ ወጣቶች እና አማኞች ከዘመኑ ፈተና በመራቅ፤ ከዝሙት፣ ከክፋት፣ ከአላስፈላጊ ተግባር በመራቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ መልካም ተግባራትን በመፈጸም ጾሙን ማከናወን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ቅንነት እና ፍቅርን፤ አብሮነት እና አንድነትን፤ ሰላም እና መተሳሰብን በማጽናት የሃይማኖት እሴቶችን በተግባር እንዲገልጡም አስገንዝበዋል።
በጾም ወቅት ስለ ሀገር ስላም እና አንድነት መጸለይ ያስፈልጋል ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ አማኞች ሰላምን በማጽናት በኩል የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ወጣቶች ራሳቸውን ከጥፋት በማራቅ ሰላምን ወደ ውስጣቸው እንዲያሰርጹም መክረዋል።
ያለ ሰላም ሃይማኖታዊ ተግባራትን መከወን አይቻልም ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ አማኞች ስለ ሀገር አንድነት ከመጸለይ ባለፈ በተግባር ሰላምን እንዲያረጋግጡም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
