የክልሎች የጋራ ገቢዎች ድርሻ እየጨመረ መጥቷል።

5
አዲስ አበባ: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢ ቋሚ ኮሚቴ አሠራር ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም ለዓመታት ሲያገለግል የነበረውን የጋራ ገቢዎች ቀመርን ማሻሻያ በማድረጉ የክልሎች የጋራ ገቢዎች ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
የጋራ ገቢዎች አሰባሰብ እና አፈጻጸም ተግባራዊ መደረግ የክልሎችን የጋራ ገቢ ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረው የተናገሩት አፈጉባኤው የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር ከመሻሻሉ በፊት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብቻ ከጋራ ገቢዎች ለክልሎች ሲተላለፍ እንደነበር አንስተዋል።
ቀመሩ ከተሻሻለ በኋላ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ለክልሎች ብቻ 91 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር ከጋራ ገቢዎች መተላለፉን ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም በሰባት ወራት አፈጻጸም 71 ነጥብ 33 ቢሊዮን ብር ለክልሎች መተላለፉንም አብራርተዋል፡፡
በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ተጨማሪ ግብዓቶችን በማሰባሰብ እና የታዩ ችግሮችን በመገምገም በቀጣይ መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እና የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባም በመድረኩ ተመላክቷል።
የፌደራል እና የክልሎች የጋራ ገቢዎች አካል የኾነው ከከፍተኛ ማዕድን እና ፔትሮሊየም ሃብቶች ልማት የሚሰበሰቡ የሮያሊቲ ገቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻሻያ እያሳየ መምጣቱም ተገልጿል።
ክልሎች ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በጋራ እየሠሩት ያለውን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“የዲፕሎማሲ ስኬት የሚመጣው የሀገር ብሔራዊ አቅም ሲጠናከር ነው” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
Next articleነብስን በስጋ ላይ ያሠለጥናሉ፤ ሰለ ሀገር ሰላም ይጸልያሉ።