
ባሕር ዳር: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዲፕሎማሲ በሀገራት እና በድርጅቶች መካከል የሚደረግ የሰላማዊ ግንኙነት፣ የድርድር እና የውይይት ጥበብ እንደኾነ ይገለጻል። ጦርነትን በማስቀረት እና ግጭቶችን በንግግር በመፍታት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ጉልህ ዓላማም አለው።
ኢትዮጵያ በሰላም አብሮ በመኖር እና በጋራ እድገት ላይ የተመሠረተ፤ በረጅም ዘመን የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ እና ልምድ ያላት ሀገር ናት። ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር፣ ሉዓላዊነትን እና የግዛት አንድነትን መጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ መርኽ እንደኾነ ይነሳል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋርም በጋራ እድገት እና ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የዲፕሎማሲ አካሄድን ትከተላለች። በዚህ ልምዷ እና መርዃም በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች።
ኢትዮጵያ በቅርብ ወራት በዲፕሎማሲው መስክ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ከማጠናከሯም በተጨማሪ በአሕጉራዊ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተሰሚነትም ከፍ የሚያደርጉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን እያደረገች ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባል እና በአውሮፓ ኅብረት የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እና የኢትዮጵያ የፓርላማ ወዳጅነት ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የተካሄዱ ለውጦች እና የመጡ ስኬቶች በዲፕሎማሲው መስክ ውጤት እንዲመዘገብ አስችለዋል ብለዋል።
የዲፕሎማሲ ስኬት የሚመጣው በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊ እና በሌሎችም ዘርፎች የሀገር ብሔራዊ አቅም ሲጠናከር እንደኾነ ነው የገለጹት። እነዚህ ብሔራዊ አቅሞችም እየተጠናከሩ በመኾናቸው በዲፕሎማሲው መስክ ጥንካሬ እና የተሻለ ተደማጭነት እንዲመጣ አድርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መኾኗ፤ በብሪክስ ጉባኤ መሪዎች ከበርካታ ሀገራት እና ድርጅቶች መሪዎች ጋር ውጤታማ ውይይቶች እና ስምምነትቶች መደረጋቸው፤ የአፍሪካ ኅብረት እና የአፍሪካ -ጣሊያን ጉባኤ በአዲስ አበባ በስኬት መካሄዱ ለመጣው ውጤት ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው እና የተስተናገዱበት አግባብ በአጠቃላይ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የተደረጉ ግንኙነቶች የዲፕሎማሲው ስኬት አመላካች እንደኾኑ ነው የገለጹት። ይህም የኢትዮጵያን የግንኙነት አድማስ የሚያሰፋ፤ የዲፕሎማሲውን አውድ የሚየቀይር እና የዲፕሎማሲ ከፍታን የሚያመጣ መኾኑን ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳዎች አሏት ያሉት አምባሳደሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንደኛው ነው ብለዋል። እንደ ባሕር በር፣ ኒውክለርን ለሰላማዊ ዓላማ መጠቀም፤ በአፍሪካ ትልቁን አየር መንገድ መገንባት፣ የነዳጅ ማጣሪያ እና የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ እና ሌሎች ኢትዮጵያ እየሠራችባቸው የሚገኙ ብሔራዊ ጥቅሞች ናቸው ነው ያሉት።
በታሪክ፣ በመልክዓ ምድር፣ በሕዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ምክንያቶች ለኢትዮጵያ የባሕር በር አስፈላጊ ነው ብለዋል። ጉዳዩ ወቅታዊ አጀንዳ ኾኖ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። የአሁኑ ትውልድም አጀንዳ አድርጎት እየተንቀሳቀሰ ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ እድገት፣ ሰላም እና መረጋጋት የጎረቤት ሀገራትም በመኾኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለኢትዮዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለጎረቤት ሀገራትም የሚጠቅም እንደኾነ አንስተዋል። በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የምሥረታ ማዕቀፍ እና በመሳሰሉት አመክንዮዎችም የባሕር በር መጠቀም እና አብሮ መሥራት አስፈላጊ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የወዳጅ ሀገራት አስፈላጊነቱን ተገንዝበው እንዲደግፉ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት አምባሳደር ዲና ሀገራት የኢትዮጵያን ጥያቄ በአወንታዊ መልኩ እየተቀበሉት መኾኑን ገልጸዋል።
ጎረቤት ሀገራት እንዲተባበሩ የዲፕሎማሲ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል ይገባልም ብለዋል። ሰላማዊ በኾነ መንገድ ጥያቄው መልስ እንዲያገኝም ማስረዳት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
ሀገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ መቀበል የጀመሩት በዲፕሎማሲ መስክ በተሠራው ውጤታማ ተግባር ነው ብለዋል። ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
