“አየር ወለዶች የኢትዮጵያ ልዩ ስጦታዎች ናቸው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

18

 

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በሐዋሳ ከተማ ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሐዋሳ የኢትዮጵያ ሁነኛ ራዕዮች የሚበሰሩባት፣ በውስጥ የመከርነውን፣ በቤት የሸሸግነውን የምንገልጥባት ናት ብለዋል። በተደጋጋሚ ያለምነውን የተናገርንባት፣ ስናሳካም በጋራ ድል ያበሰርንባት ቦታ ስለኾነች ለሲዳማ ሕዝብ በተለይም ቄጠላን ላቆዩን አባቶች ምስጋና አቅርባለሁ ነው ያሉት።

ሐዋሳ ብርሃን ኾና ስላየናት የተሰማኝን ደስታ ልንገልጽ እወዳለሁ ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ብርሃን የኾነችውን ሐዋሳን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።

የሰው ልጅ ከእናት እና ከአባቱ ደም እና ዘር ተጋርቶ ይወለዳል፣ የሰው ልጅ ከሀገሩ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ማንነት ተጋርቶ ይወለዳል፤ የዛሬ አየር ወለዶች ደግሞ ከእናት ከአባታቸው፣ ከድንቂቷ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው ብለዋል። ከአየር የተወለዱ የኢትዮጵያ ልዩ ስጦታዎች ናቸው ነው ያሉት።

ቀይ መለዮ የለበሱ፣ ከአየር ተምዘግዝገው የሚወርዱ ባለሁለት ክንፍ አየር ወለዶች፣ በአንደኛው ክንፍ ዓላማ፣ በሌላኛው ክንፍ ሥነ ምግባር አንግበው ከአየር የሚወርዱ፣ ውጊያ የሚያስቀሩ፣ ውጊያ የሚጨርሱ፣ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል የኾነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቃችንን በድል የሚያውለበልቡ ጀግኖች ስለኾኑ የሚገባቸውን ክብር እንሰጣቸዋለን ነው ያሉት።

የእኛ ተልዕኮ ራዕይ ያለው፣ ለትውልድ የሚሸጋገር ሁነኛ ተቋም መፍጠር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእኛ ተልዕኮ ውጊያ የሚያስቀር፣ ውጊያ የሚጨርስ ኃይል መገንባት ነው፣ የእናንተ ተልዕኮ ኢትዮጵያን መገንባት፣ ኢትዮጵያን መጠበቅ፣ ኢትዮጵያን ማጽናት እና ኢትዮጵያን ማሸጋገር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ ትሠራለች፣ ኢትዮጵያ በልጆቿ አጥንት እና ደም ትጸናለች፣ ኢትዮጵያ አልተደፈረችም፤ አትደፈርም፤ በክብር እና በነጻነት ለልጆቻችን የምናሸጋግራት ብቸኛዋ የአፍሪካ ፈርጥ ኾና ትቀጥላለች ነው ያሉት።

የእኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላም ለማረጋገጥ፤ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፤ በቀጣናችን ላሉ ሀገራት መከታ፣ አለኝታ ጋሻ ለመኾን ነው ብለዋል።

በምድር፣ በተራራ፣ በዥረት የነበረውን ሥልጠና ወደ ባሕር ያሸጋገርነው ከውኃ የመራቅ፣ ከውኃ የመሸሽ፣ ውኃን እንደ ባዕድ አምልኮ የማየት ክፉ ልማዳችን አሁን ባለው የልማት እሳቤ ውኃ ሕይወት፣ ውኃ ልማት መኾኑን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ከሶማሊያ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባሕር የሚያጋጥሙ ሽብሮችን ለማስቀረት፣ ልማት እና ብልጽግናን በቀጣናው ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለቀጣናው የሚኾን ሠራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሠራዊት ስለገነባች የምሥራቅ አፍሪካ፣ ድፍን የአፍሪካ ሀገራት እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት። ተቋም፣ አስተማማኝ ሠራዊት የምንገነባው በቀጣናችን ውጊያ እና ሽብር እንዳይፈጠር ነው፤ ቢፈጠርም በአጠረ ጊዜ ለመቋጨት ነው ብለዋል።

የተገነባው ኃይል ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ዓለም አቀፍ ስምሪቶች ስመጥር ተግባራት ሲፈጽም እንደኖረው ሁሉ በዚህም ዘመን ያንን ታሪክ የሚደግም፣ የቀይ መለዮ ክብር የገባው፤ ለባንዲራ፣ ለሀገር ክብር ነጻነት ራሱን የሚሰዋ፣በአዕምሮም በአካልም የበለጸገ፣ ቴክኖሎጂን የሚያጫውት፣ የሚጠቀም፣ ውጊያን የሚሠራ፣ የሚጨርስ መኾኑን አንስተዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ነጻነት፣ የአፍሪካን ሰላም የሚያስከብር አስተማማኝ ኃይል መኾኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብልጽግና ይረጋገጣል፤ የኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪነት እና ምሳሌነት ይረጋገጣል፤ ለልጆቻችን፣ ለመላው አፍሪካ ኩራት የኾነችን ኢትዮጵያን እናስረክባቸዋለን ብለዋል።

ይህ የሚኾነው በዋዛ ፈዛዛ አይደለም፤ ላባችን አንጠፍጥፈን፣ ደማችን አፍስሰን፣ አጥንታችን ከስክሰን ኢትዮጵያን እንገነባለን፤ አፍሪካን እንገነባለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሙያን ለባለቤቱ ብንተውለትስ?