“የእኛ ሠራዊት የተግባር እንጂ የንድፈ ሃሳብ አይደለም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

8

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከለካያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው።

በክብረ በዓሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ከውስጥ እና ከውጭ የተቃጡባትን የውክልና ጥቃቶች እየመከተች እዚህ መድረሷን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የትልቅ ሀገር ባለቤት እና የትልቅ ሕዝብ ሀገር ባለቤቶች ነን ብለዋል። የሀገር መከለከያ ሠራዊት ኢትዮጵያውያን በሚመጥን መልኩ መገንባቱን ገልጸዋል። ሠራዊት የማንም የፖለቲካ እና የብሔር ውግንና የሌለው መኾኑን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ዘመናዊ ሠራዊት መገንባቱንም ገልጸዋል። የተሠራው ሥራ የሚያስደንቅ መኾኑን ተናግረዋል። የተቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት ሁለገብ እና አስተማማኝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

ሀገር እና የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ያልገባቸው ተቀጣሪ ባንዳዎች እያስቸገሩን፣ እነሱን እየታገልን የሠራነው የሠራዊት ግንባታ ሥራ ስለኾነ ድካማችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል ነው ያሉት። እየተዋጋን የገነባው ሠራዊት በጦርነት ሂደት የተፈተነ ነው ብለዋል።

“የተፈጠረውን ግጭት በጦርነት ተሞክሮ የሠለጠነ ሠራዊት እንዲኖር አድርጓል፤ የእኛ ሠራዊት የተግባር እንጂ የንድፈ ሃሳብ አይደለም” ነው ያሉት። የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ራሱን በማባዛት ጠንካራ ኃይል የገነባ መኾኑን ገልጸዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሠራዊት አባላት የተሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት በመፈጸም ሀገር እና ሕዝብ ማኩራታቸውንም ተናግረዋል። ወደፊትም ግዳጃቸውን እየተወጡ ሀገራቸውን ለማኩራት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የልዩ ዘመቻዎች እዝ ባለፉት ዓመታት አስደማሚ የጀግንነት ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል። ዕዙ በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት፣ በአልሸባብ የጸረ ሽብር ተጋድሎ፣ የሰሜን ዕዝ ክህደት ሲፈጸምበት የመመከት እና በሌሎች ግዳጆች አስደናቂ ጀብዱ የፈጸመ ጀግና መኾኑን ተናግረዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ጦርነት ቀያሪ የጀግኖች ስብስብ ነው ብለዋል። ጀግኖቹ እንኳን ለዚህ ቀን አበቃችሁ፤ ለኢትዮጵያ የከፈላችሁት መስዋዕትነት በታሪክ የተመዘገበ ነው፤ ጠላቶቻችን ያራደ፣ የኢትዮጵያ የጀግንነት ማሳያ ናችሁ ብለዋቸዋል።

የቀይ መለዮ ክብራችሁን ጠብቃችሁ፣ የላቀ ሥራ ለመሥራት እና ኢትዮጵያ ፍጹም ሰላማዊት የበለጸገች ሀገር ለመኾን እያደረገችውን ያለችውን ትግል በድል ለመጨረስ ዛሬም እንደ ትናንቱ በጽናት እንደምትቆሙ እናምናለን ነው ያሉት።

ለእናት ሀገራችን ክብር በጽናት እንታገላለንም ብለዋል በመልዕክታቸው።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጀግንነት ትናንትም ነበር፣ ዛሬም ቀጥሏል፤ ዛሬ ግን በትናንትናው ስልት አንሄድም” ሌትናል ጄኔራል ሹማ አብደታ
Next articleሙያን ለባለቤቱ ብንተውለትስ?