“ጀግንነት ትናንትም ነበር፣ ዛሬም ቀጥሏል፤ ዛሬ ግን በትናንትናው ስልት አንሄድም” ሌትናል ጄኔራል ሹማ አብደታ

15

 

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ መሪዎች በመድረኩ ላይ ተገኝቸዋል።

በዕለቱ መልዕክት ያስተላለፉት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ እና የዓድዋ ድል ከፍተኛ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ሌትናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በዓሉን ማክበር ያስፈለገው የሠራዊቱን የ65 ዓመታት ጉዞ እና በቅርብ የተደረገውን የተቋሙ የለውጥ ሥራ በአንድ ላይ በመደመር ለቀጣይም መልክ ለማስያዝ ነው ብለዋል።

የሠራዊቱን አሁናዊ ቁመና በማመላከት ለሕዝባችን መመኪያ እና መከታ፤ ለሀገራችን ጠላት ደግሞ መቅሰፍት መኾናችንን ለማሳየት እንደኾነ ነው የገለጹት።

የሀገራችን ጠላቶች አርፈው እንዲቀመጡ፤ ካልኾነ ግን ውጊያ ጨራሽ አቋም እንዳለን እንዲረዱም እንፈልጋለን ነው ያሉት።

“ጀግንነት ትናንት ነበር፣ ዛሬም ቀጥሏል፤ ዛሬ ግን በትናንትናው ስልት አንሄድም” ነው ያሉት። የዛሬው በዓልም የትላንቱን ልምዳችን ከዛሬው የሠለጠነ አስተሳሰባችን ጋር አዋሕደን ለመራመድ የምንጠቀምበት ነው ብለዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ምስረታ ከአንድ ሻንበል ተነስቶ ዛሬ ካለበት ቁመና ላይ የደረሰው በዋዛ አይደለም፤ ይልቁንም የሥልጠና ማዕከሉ በአዲስ ተደራጅቶ፣ የሥልጠና አሰጣጥ ሥርዓቱንም በማዘመን እንደኾነም ተናግረዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከመቸውም ጊዜ በላይ የሠለጠነ፤ በባሕርም ይሁን በየብስ የትኛውም መልክዓ ምድር የማይበግረው ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የምድር ድሮንነት እና የውጊያ ማርሽ ቀያሪነታችንን አስቀጥለን ሕዝባችን የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ ለመፈጸም ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article👉 ውብሸት ወርቃለማሁ
Next article“የእኛ ሠራዊት የተግባር እንጂ የንድፈ ሃሳብ አይደለም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ