👉 ውብሸት ወርቃለማሁ

12

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሙያ ፈርቀዳጅ ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ በ1934 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በመንዝ ማፉድ ነው የተወለዱት።

በቤተክኅነት ትምህርት ቢያድጉም ገና በልጅነታቸው በማፉድ ገበያ ረጅም ሰው ትከሻ ላይ በመውጣት ለግብይት የሚረዱ መረጃዎችን በማስተላለፍ የመጀመሪያውን የማስታወቂያ ሥራ በዚህ ሳምንት የካቲት 15/1949 ዓ.ም እንደጀመሩ ይነገርላቸዋል።

ቤተሰቦቻቸው በወቅቱ ሥራውን “የጨዋ ልጅ በገበያ አይጮኽም” ብለው ቢገስጿቸውም እርሳቸው ግን የጀመሩትን የፈጠራ መንገድ በመከተል ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው መደበኛ ትምህርታቸውን ከሥነ ጥበብ ሙያ ጋር አቀናጅተው ለመቀጠል በቅተዋል።

በሙያ ሕይወታቸው በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት እስከ ምክትል ዳይሬክተርነት የደረሱት ጋሽ ውብሸት፣ በርካታ ድራማዎችን በመድረክ እና በቴሌቪዥን ማቅረብ ችለዋል።

በኋላም በብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት ውስጥ በማስታወቂያ ባለሙያነት የሠሩ ሲኾን፣ “አንበሳ ማስታወቂያ” የተባለውን ተቋም በመመሥረት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እና አሻራቸው ያረፈባቸውን የማስታወቂያ ሥራዎች ለዛ ባለው እና በሚያስገመግመው ድምጻቸው ለሕዝብ አድርሰዋል።

ከሙያዊ ስኬታቸው ባሻገር ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ በሀገራዊ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ማለትም በቻምበር ኦፍ ኮሜርስ አመራርነት እንዲሁም በቀይ መስቀል እና ደም ባንክ አምባሳደርነት በቅንነት አገልግለዋል።

ለእንግድነት ሲጠሩ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የተዋበ ነጭ ልብስ እና ካባ ማዘውተራቸው እና ለወጣት ባለሙያዎች አርዓያ መኾናቸው የሚታወስ ሲኾን በተለያዩ ዘርፎች ላበረከቱት አስተዋጽኦም በርካታ ሽልማቶችን እና ዕውቅናዎችን ለመጎናጸፍ በቅተዋል።

ምንጭ፡- የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ግለታሪክ ማስታወሻ

👉 አርበኛ ስምኦን አደፍርስ

ጀግናው የታክሲ ሹፌር ስምኦን አደፍርስ የሀገር ፍቅር እና የጀግንነት ተምሳሌት የነበሩ አርበኛ ናቸው። በ1905 ዓ.ም በሐረርጌ ተወልደው አዲስ አበባ ካደጉ በኋላ በዘመኑ ብርቅ በነበረው የታክሲ አሽከርካሪነት ሙያ ተሰማርተው ይኖሩ ነበር።

ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የግፍ አገዛዙን ያልተቀበሉት ስምኦን አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ ለወሰዱት ታሪካዊ እርምጃ የጀርባ አጥንት በመኾን በምስጢር አብረዋቸው አቅደዋል፤ የቦምብ መወርወር ልምምድም በዝቋላ ደብር አብረው አከናውነዋል ይላል ታሪካቸው።

በዚህ ሳምንት የካቲት 12/1929 ዓ.ም አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም በጠላት ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ሲወረውሩ ስምኦን አደፍርስ በታክሲያቸው ቤተ መንግሥት ደጃፍ ላይ በንቃት ይጠብቋቸው ነበር።

እርምጃው እንደተወሰደ እና ከፍተኛ ትርምስ እንደተፈጠረ ሁለቱን አርበኞች በመኪናቸው ጭነው በጠላት መትረየስ ሳይበገሩ ሾልከው በማምለጥ እስከ ፍቼ ድረስ በሰላም አድርሰዋቸዋል። ይህ የጀግንነት ተግባራቸው በወቅቱ ለአርበኞች ትልቅ ተስፋ የሰጠ እና የጠላትን ቅስም የሰበረ ድርጊት ነበር።

ከክስተቱ ከአንድ ሳምንት በኋላ በጠላት እጅ የወደቁት ስምኦን አደፍርስ ማንኛውንም አይነት ስቃይ እና መከራ ቢቀበሉም ምስጢር ባለማውጣት ጽናታቸውን አስመስክረዋል። አሰቃዮቻቸው የፈለጉትን መረጃ ማግኘት ባለመቻላቸው እንዲገደሉ አድርገዋል።

ስምኦን አደፍርስ ለሀገር ነጻነት ሲሉ የገዛ መኪናቸውን እና ሕይወታቸውን የሰጡ፤ በታሪክ መዝገብ ስማቸው በደመቀ ሁኔታ የሚታወስ ታላቅ አርበኛ ናቸው።

ምንጭ ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

👉የባንክ ቼክ አጀማመር

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በእጅ ተጽፎ የተፈረመው የባንክ ቼክ በዚህ ሳምንት የካቲት 9/1651 ዓ.ም በለንደን የተጻፈ ሲኾን የ400 ፓውንድ ክፍያ የያዘ ሰነድ ነበር።

ይህ ሰነድ በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ በዌስትሚኒስተር አቢ ለጉብኝት ተቀምጦ ይገኛል። ቼኩ በኒኮላስ ቫናከር ተፈርሞ ለክቡር ዴልቦ እንዲከፈል የታዘዘ ሲኾን “ቼክ” የሚለው ስያሜም በ1700ዎቹ በሰነዶቹ ላይ የሚደረጉ ተከታታይ ቁጥሮችን ለመቆጣጠር ወይም ለመፈተሽ ከነበረው ልምድ እንደመነጨ ይገመታል።

ቼኮቹ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ሲጀምሩ ባንኮች ክፍያ ለመሠብሠብ ይገጥማቸው የነበረውን የመጓጓዝ ችግር ለመቅረፍ “ክሊሪንግ ሀውስ” የተባለው ሥርዓት በአንድ የለንደን ቡና ቤት ውስጥ በድንገት ተፈጠረ።

ሁለት የባንክ መልዕክተኞች በቡና ቤት ተገናኝተው እርስ በርሳቸው የሚፈለጉባቸውን ቼኮች እዚያው በመለዋወጥ ትርፍ ጉዞን ለማስቀረት የጀመሩት ልምድ እያደገ በመሄድ እስከ ዛሬ ድረስ ባንኮች እርስ በርሳቸው “ቼክ” የሚለዋወጡበትን ዓለም አቀፍ አሠራር ሊወልድ ችሏል።

ምንጭ፦ ዚስደይ ኢን ሂስትሪ

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሀገር ዕድገት የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን የደባርቅ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
Next article“ጀግንነት ትናንትም ነበር፣ ዛሬም ቀጥሏል፤ ዛሬ ግን በትናንትናው ስልት አንሄድም” ሌትናል ጄኔራል ሹማ አብደታ