
አዲስ አበባ፡ የካቲት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የታነፀ፣ በፈጠራ ሥራ የተካነ እና ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅዖ የሚያበረክት የወጣት ትውልድ ለመፍጠር ያለመው “የኢትዮ-ዓለም አቀፍ የሳይንስ እና ትምህርት የወጣቶች ፌስቲቫል” ዛሬ ተጀምሯል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ይህንን መድረክ የከፈቱት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚኾነው ወጣት መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ኀይል ላይ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ኢንቨስት ማድረግ የሀገሪቱን የዕድገት ጉዞ እንደሚያፋጥነው አስገንዝበዋል።
በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ ፌስቲቫል በርካታ ፋይዳዎች ያሉት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት ወጣቶችን ከዓለም አቀፍ የዕውቀት ዑደት ጋር የሚያገናኝ እና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ መፍጠር ይገባል።
በመድረኩም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት እና ሌሎች የደረሱበትን ደረጃ የሚመለከቱበት ዕድል መመቻቸቱንም አብራርተዋል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ብቁ እና ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
“ዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ የተንሰራፋበት በመኾኑ በቀጣይ የሳይንስ ሰመር ካምፖችን በማዘጋጀት የሀገራቸውን ስም የሚያስጠሩ ብቁ ወጣቶችን ለማፍራት በትኩረት እንሠራለን” ብለዋል ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ።
ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ከአሜሪካ እና ካናዳ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ምሁራን እና መሪዎች፣ ከአዲስ አበባ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።
ይህ ፌስቲቫል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማሳካት እና ወጣቶች በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ለማስቻል ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
